አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ሥልጠና ለሳይበር ደህንነትና ሉዓላዊነት ትልቅ አሻራ የሚጥል ነው አሉ የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፡፡
5ኛው ዙር የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ቻሌንጅ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፡፡
ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ስልጠናው ለሀገሪቱ የሳይበር ደህንነት እና ሉዓላዊነት ትልቅ አሻራ የሚጥል ነው፡፡
የሀገር ሉዓላዊነት ወደ ዲጂታል ምሕዳር በተስፋፋበት በዚህ ወቅት ራስን ማብቃት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የሰው ኃይልን ማብቃት ላይ እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ ÷ ለተሳካ የሳይበር ከለላ ትግበራ አዳጊዎች ላይ መሰረት ያደረገ ልማት ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ቴክኖሎጂ ላይ መሰረት ያደረገ ልማት ለሀገር ዘላቂ ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ፕሮግራሙ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሀገሪቱን የሳይበር ደህንነት እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በማለም የተዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በዘርፉ ብቁ የሆኑ ወጣቶችን እያፈራ የሚገኘው የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ቻሌንጅ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ አዳጊዎች እና ወጣቶች የሚሳተፉበት ነው።
ለስልጠናው የተመዘገቡት ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎች ሲሆኑ ÷ ከእነዚህ ውስጥ የተመረጡት 1 ሺህ 249 አዳጊዎች አሁን ስልጠናውን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።
በአሸናፊ ሽብሩ

