Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የምክክር ጉባኤው በአንድነቷ የጸናች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ መልካም አጋጣሚ ነው – ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምክክር ጉባኤው በአንድነቷ የጸናች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ መልካም አጋጣሚ ነው አሉ ተመካካሪዎች፡፡
ከተመካካሪዎቹ መካከል አባገዳ ለሜቻ ለማ እንዳሉት፤ በምክክሩ ላይ የተለያዩ ሀሳቦች በነፃነት እየቀረቡና እየዳበሩ ይገኛሉ።
በምክክሩ ሁሉም ተመካካሪ ሀሳቡን በነጻነት እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ይህም በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍታት የሚያስችል የመፍትሔ ሀሳብ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የጋራ መግባባት የተፈጠረባትና በአንድነቷ የጸናች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ባዬ በሬ በበኩላቸው፤ ምክክሩ ከአካታችነት አንጻር ሁሉንም የሚያሳትፍና የሀሳብ ብዝሃነት የሚንጸባረቅበት ነው ብለዋል፡፡
በምክክሩ ላይ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ሀሳቦች እየቀረቡ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የምክክር ሂደቱ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በሚወክል መልኩ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አለሙ አሻግሬ (ዶ/ር) ናቸው።
ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በምክክር የመፍታት አዲስ ባህል መሆኑን ገልጸው፤ ሂደቱ ዛሬ ላይ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ የምትሆን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የሀሳብ ብዝሃነትን በማንጸባረቅ ለጋራ መግባባትና ለዘላቂ ሰላም መሠረት የሚጥል ተስፋ ሰጪ ሂደት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
Exit mobile version