Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ምክክሩ የጋራ መግባባትን በማጎልበት ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ሰፊ ዕድል ከፍቷል – ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጋራ መግባባትን ለማጠናከርና የተሻለች ሀገርን ለመገንባት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የታሪክ ድልድይ ነው አሉ የምክክሩ ተሳታፊዎች፡፡

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ ላይ 4 ሺህ የሕዝብ ወኪሎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።

የጉባኤው ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፥ ምክክሩ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል መግባባት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር ወደ መፍትሄ ለመቅረብ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ይህ ታላቅ ሁነት ባሳለፍነው የጦርነት ታሪክና አለመግባባትን በምክክር በመፍታት ሰላሟ የተረጋገጠና የልማት ጎዳና ላይ ባለችው ኢትዮጵያ መካከል ልዩ የታሪክ ድልድይ መሆኑን አውስተዋል።

ምክክሩ ከተለያየ አስተሳሰብና የአኗኗር ዘዬ የመጣውን ማህበረሰብ እርስ በእርስ የመተዋወቅ እድልን አስፍቷል ነው ያሉት።

ሌላኛዋ ተመካካሪ ሜሪ ደስታ በበኩላቸው፤ በምክክሩ ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን በነፃነት ለመግለጽ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
ምክክሩ ለትውልዱ አንድነቷ የተጠናከረና የበለጸገች ሀገር የምናሻግርበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ምክክሩ ከአጀንዳ አሰባሰብ ጀምሮ አሁን እስካለበት ሂደት ድረስ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች አካታችና አሳታፊ ያደረገ እንደነበር የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ አብርሀም ሀይሌ ናቸው።

Exit mobile version