Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የዘገየ የፍትህ እና የብሔራዊ ጥቅም ጥያቄ ነው

የኢትዮጵያ የባህር በር አልባነት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የንግድ ልውውጥ እና ብሔራዊ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመደመር መንግሥት እና የኢትዮጵያ ህዝብ እያነሱት ያለው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የህልውና፣ የልማት እና የፍትሃዊነት ጥያቄ ነው።

ይህ ጥያቄ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም እና መብት ከማስከበር የሚነጭ እንጂ የሌሎችን ሉዓላዊነት ወይም ብሔራዊ ክብር ለመንካት የሚደረግ ጥረት አይደለም።

የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከዓለም አቀፍ ህጎች እና ከታሪካዊ እውነታዎች ጋር የተያያዘ ህጋዊ ጥያቄ ነው።

ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት እና በዓለም ላይ በህዝብ ቁጥር ትልቋ ወደብ አልባ ሀገር ናት።

እንዲህ ያለ ግዙፍ ህዝብ እና ኢኮኖሚ ያለው ሀገር ሙሉ በሙሉ በሌሎች ሀገራት ወደቦች ላይ ጥገኛ መሆኑ የረጅም ጊዜ ዕድገትን ይገድባል።

ስለዚህ የባህር በር ጥያቄው የኢኮኖሚ ነጻነትን የማረጋገጥ፣ የወደብ ኪራይ ወጪን በመቀነስ ለሕዝብ ልማት የማዋል፣ የዓለም አቀፍ የባህር ህግ ስምምነቶች ለወደብ አልባ ሀገራት የሰጡትን መብት የመጠቀም ፍላጎት ነው።

ኢትዮጵያ ጥያቄውን የምታቀርበው በሰላማዊ መንገድ፣ በዲፕሎማሲያዊ ድርድር እና በጋራ ጥቅምና ስምምነት ላይ ተመስርታ ነው።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሉዓላዊነት መብት እና የብልጽግና ማረጋገጫ፤ የዘገየ የፍትህ እና የብሔራዊ ጥቅም ጥያቄ ነው።

ሀገሪቱ በባህር በር እጥረት ምክንያት እየከፈለች ያለውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የደህንነት ዋጋ ለመቀነስ የምታደርገው ጥረት የሉዓላዊ መብቷ መገለጫ ነው።

ይህ ፍላጎት የጎረቤቶቿን ክብርና ጥቅም የሚጋፋ ሳይሆን፣ በቀጣናው ላይ የጋራ ብልጽግናን እና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የሚያስችል የትብብር ጥሪ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።

Exit mobile version