Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከውጪ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ስራ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍና ሀገራዊ ኢኮኖሚን በራስ አቅም ለመገንባት በግብርናው ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤት አመጥተዋል አሉ የምጣኔ ሀብት ምሁራን።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር መስፍን መኮንን (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከውጪ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እያከናወነች የምትገኘው ስራ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡
በግብርናው ዘርፍ ስንዴ፣ ሩዝ እና መሰል ሰብሎችን በሀገር ውስጥ በስፋት በማምረት ሀገር ታጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ በመታደግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቆጣጠርና የሀገርን ኢኮኖሚ በራስ አቅም ለመገንባት 96 አይነት ምርቶች ተለይተው በሀገር ውስጥ ማምረት በመቻሉ 5 ቢሊየን ዶላር ማትረፍ ተችሏል ያሉት ደግሞ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትንተና ባለሙያ ተሾመ እሸቱ ናቸው።
በግብርናው ዘርፍ በተለይም በብዛት ከውጪ ይገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉ በዘርፉ የተገኘ አበረታች ውጤት ነው ብለዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ በመቻሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ሌሎች ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸው ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ ማለቱ በዘርፉ የተገኘ አበረታች ውጤት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረጓ በኢንዱስትሪ ግብዓት እና ኃይል አቅርቦት ዘርፍ ላይ ትልቅ ውጤት እንዲመዘገብ አስችሏል ነው ያሉት።
ዘርፉ የጥሬ እቃ አቅርቦትን ማሳደግ፣ የፋይናንስ ተቋማት ብድርን በአነስተኛ ወለድ ማቅረብ፣ የማምረቻ ቦታዎችን እና ሼዶችን ማዘጋጀት እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን ማሟላት መወሰድ ያለባቸው ማሻሻያዎች መሆናቸውን ምሁራኑ ጠቁመዋል።
የግብርናው ዘርፍ በዝናብ ላይ ጥገኛ መሆኑን ያነሱት ምሁራኑ የምርት መጠኑን ዘላቂ ለማድረግና ምርታማነትን ለመጨመር የከርሰ ምድር ውሃ አጠቃቀምንና ዘመናዊ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በወርቅአፈራው ያለው

 

Exit mobile version