በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው የዲጂታል የፋይናንስ ግብይት እና የገንዘብ ዝውውር የቴክኖሎጂ ምጥቀት የሀገራትን የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ መዋቅር እየቀየረ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ይህንን ለውጥ በመገንዘብ ዲጂታል 2025ን ሙሉ በሙሉ አሳክታ፣ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ቀርጻ ወደ ተግባር ገብታለች፡፡
በዚህ ረገድ የአህጉራችንን ሀገራት ስናይ፣ ወደ ዲጂታል የፋይናንስ ግብይት እና የገንዘብ ዝውውር ሙሉ በሙሉ የገቡ እና ሥርዓቱን ያዘመኑ ሀገራት ቁጥር አሁንም ቢሆን ጥቂት ነው። ሆኖም ግን በዚህ ዘርፍ ላይ ጠንካራ መሠረት ጥለው ለሌሎች አርአያ እየሆኑ ያሉ ጥቂት ሀገራትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ኬንያ በኤም-ፔሳ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ሥርዓት የፋይናንስ አካታችነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ተሞክሮ ያላት ሀገር ናት። ናይጄሪያ በበኩሏ በግል ተቋማት መስፋፋት እና በዲጂታል ባንኪንግ ሥርዓት በአህጉሪቱ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ካላቸው ሀገራት አንዷ እየሆነች ነው፡፡ ሩዋንዳ የመንግሥት አገልግሎቶችን “ኢሬምቦ” በተሰኘው የዲጂታል መድረክ በማገናኘት እና ክፍያዎችን በዲጂታል ፋይናንስ በመደገፍ ጥሩ ሥራ እየሠራች ነው፡፡
ከዚህ አንጻር የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ገና በጅምር ደረጃ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የሄደችበት ፈጣን ርቀት እና የገበያ ስፋት በአህጉሪቱ አስደናቂ እና ተጠቃሽ ያደርጋታል።
በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በሀገሪቱ የታየው የዲጂታል ፋይናንስ ዕድገት፣ ሀገሪቱ ያስቀመጠችውን ታላቅ ራዕይ በፈጣን ሁኔታ እያሳካች ለመሆኗ ግልጽ ማሳያ ነው።
ይህ ሽግግር የፋይናንስ ሥርዓቱን ከማዘመን ባለፈ፣ የጥሬ ገንዘብ ንክኪን በመቀነስ እና የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ መሠረት እየጣለ ይገኛል። በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የነበረው የገንዘብ አያያዝ እና የግብይት ባህል በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል።
ቀደም ሲል የነበረው ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሬ ገንዘብ ይዞ የመንቀሳቀስ ልማድ አሁን ላይ በፍጥነት እየተቀየረ ነው። በባንኮች፣ በቴሌኮም ተቋማት እና በግል የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አልሚዎች አማካኝነት የተዘረጉት የዲጂታል መክፈያ ዘዴዎች የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት አካል ሆነዋል። ዜጎች በማንኛውም ቦታ እና ጊዜ ሆነው ግብይቶችን በስልካቸው መፈጸም በመቻላቸው የጊዜ፣ የጉልበት እና የገንዘብ ብክነትን በእጅጉ መቀነስ ተችሏል። ይህ ስኬት ኢትዮጵያ በዘርፉ የበለጸጉ ሀገራት የደረሱበትን ጥሬ ገንዘብ የማይጠቀም ወይም የ”ካሽለስ” ማኅበረሰብ ደረጃ ለመድረስ በልበ ሙሉነት እየተጓዘች መሆኑን ያረጋግጣል።
ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉን ማዘመን ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ የመንግሥታዊ አገልግሎቶችን እና የክፍያ ሥርዓቶችን ወደ ዲጂታል አማራጭ እየቀየረች ትገኛለች። ግብር መክፈል፣ የውሃና መብራት ክፍያዎችን መፈጸም፣ እንዲሁም የተለያዩ ፈቃዶችን እና ሰነዶችን ማውጣት በዲጂታል መድረኮች መደረጉ ባደጉት ሀገራት የተለመደ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ይህንን በተግባር በማሳየት ቀዳሚነቱን እየያዘች ነው።
የዲጂታል ክፍያዎች ግልጽነትና ተጠያቂነት ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና ሙስናን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
በፋይናንስ አካታችነት ቀደም ሲል የባንክ አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ በተለይም በገጠር የሚኖሩ ዜጎችን ወደ ፋይናንስ ሥርዓቱ እንዲገቡ አድርጓል።
በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ በዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍ እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን ዕድገት የሀገሪቱን የነገ ብሩህ ተስፋ አመላካች ነው። ኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓቱን ከመቀየር ባለፈ የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻሏ፣ ሀገሪቱን በአፍሪካ መድረክ የለውጥ ተምሳሌት ያደርጋታል።

