አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር አርአያ የሚሆን ነው አሉ ተመካካሪዎች።
ተመካካሪዎች እንደገለጹት ÷ በምክክር መድረኩ እየተነሱ ያሉት ሐሳቦች ሀገራዊ ሰላምን፣ ዴሞክራሲን እና አብሮነትን ለማጠናከር ጠንካራ መሠረት የሚጥሉ ናቸው፡፡
ከተመካካሪዎች መካከል ወጣት ዳንኤል ሲሳይ÷ የሀገራዊ ምክክር የእስካሁን ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ እና ትልቅ ሀገራዊ ተስፋ የሚታይበት ነው ብሏል።
ሒደቱ ሀገራዊ የትውልድ ዕጣ ፈንታን በባለቤትነት በመቅረጽ ረገድ ታሪካዊ ፋይዳ እንዳለው በመገንዘብ የሚካሄድ በመሆኑ በተለይም ለመጪው ትውልድ፣ ታዳጊዎች እና ለወጣቶች ብሩህ ተስፋን የፈነጠቀ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
አቶ ጸድቻ ሌሌ በበኩላቸው÷ መድረኩ አካታች፣ መከባበር የተሞላበት፣ ሁሉም ሰው በነፃነት ሀሳቡን የሚያንሸራሽርበት እና ጠንካራ ህብረት የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።
እያንዳንዱ ተመካካሪ ችግሮችን በምክክር መፍታት እንደሚቻል በማመንም፣ ስሜቱንና ሀሳቡን በግልጽ ያንጸባረቀበት መድረክ መሆኑን አብራርተዋል።
እየተካሄደ ያለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ሁሉንም ያሳተፈ እና የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ሰፊ ዕድል የሚከፍት ነው ያለት ደገሞ አቶ ፋራህ ወርሰመ ናቸው፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያውያን በምክክር ችግሮቻቸውን ለመፍታት በአንድነት የተሰበሰቡበት ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ በመሆኑ ከጉባዔው የሚጠበቀው ውጤትም አዎንታዊ እንዲሆን ከፍተኛ እምነት እንደሚጣልበት ተናግረዋል።
ይህ አሳታፊ የምክክር ሒደት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ጭምር የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደ መልካም ተሞክሮ እና ሞዴል ሊወሰድ የሚችል ነው ብለዋል።
በጉባኤው የተገኙት ገንቢ ውይይቶችና የተደረሱ ስምምነቶችም ለቀጣይ ሰላም፣ ዕድገት እና አብሮነትን ለማጠናከር ታላቅ ምዕራፍ የሚከፍቱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

