አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት በአምራች ኢንተርፕራይዞች ለ270 ሺህ 548 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል አለ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት፡፡
የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኑኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮቤል አሕመድ እንዳሉት፥ የአምራች ኢንተርፕራይዞችን የማምረት አቅም በማጠናከር ተኪ ምርትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህም የማምረቻ ቦታ፣ የፋይናንስና የግብዓት አቅርቦትን ከማሳካት ባለፈ የተለያዩ የተግባር ተኮር ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ኢንተርፕራይዞች ከብድርና መስሪያ ቦታ ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የዘርፉን የአሰራር ሥርዓት ለማሻሻል፣ የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግና ጥራት ያላቸው ምርቶች እንዲያመርቱ ለማስቻል አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች እንዲቋቋሙና ነባሮች እንዲጠናከሩ በትኩረት መሰራቱን ጠቁመው÷ አምራቾቹ ወጪና ተኪ ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ አስፈላጊው ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 4 ሺህ 233 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች የተቋቋሙ ሲሆን ÷ 16 ሺህ 998 አምራች ኢንተርፕራይዞችን ደግሞ ማጠናከር ተችሏል፡፡
አዲስ አምራች ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋምና ነባሮችን በማጠናከርም ለ270 ሺህ 548 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

