Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ምክክሩ ቀጣዩ ትውልድ መደማመጥን የአስተሳሰብና የኑሮ ባህል እንዲያደርግ ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው – የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክክሩ ቀጣዩ ትውልድ መደማመጥን የአስተሳሰብና የኑሮ ባህል እንዲያደርግ ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው አሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ በፖለቲካ ሥርዓት፣ በፖለቲካ ውክልናና በምርጫ ሥርዓት፣ በሙስናና በመልካም አስተዳደር፣ በሃይማኖት ጉዳዮችና በሰላም ግንባታ ዙሪያ በተካሄዱ ምክክሮች ተመካካሪዎች ባቀረቧቸው ምክረ ሀሳቦች ላይ መግባባት መደረሱን ይፋ አድርጓል።
ይህ ሂደት በተለይ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ተስፋን የሚያለመልም መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ምክክርና መደማመጥን የሚያስቀድም ሀገራዊ መድረክ ዘላቂ ሰላምን፣ ሀገራዊ መግባባትንና የጋራ የልማት ርዕይን ለመገንባት ጠንካራ መሠረት ይጥላል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪ ልዩወርቅ ሙሉጌታ ምክክርን በማስቀደም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ጥረቶች ተስፋ የሚያለመልሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የምክክር ጉባኤው የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት፣ በሰላም ግንባታና በልማት ሂደት ያላቸውን ተሳትፎ በማጠናከር ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋ የሚሰጥ የጋራ መድረክ መሆኑንም አንስተዋል።
ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ የሆኑት ንጉሥ አይጋበዝ በበኩላቸው፤ የምክክር ጉባኤው ቀጣዩ ትውልድ መደማመጥንና ምክክርን የአስተሳሰብና የኑሮ ባህል እንዲያደርግ ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡
በሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች መካከል የሚፈጠረው መግባባትና የሚቀርቡት ምክረ ሀሳቦችም በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም በመገንባት ሰላምን፣ አንድነትንና የጋራ ሀገራዊ ጥቅምን ለማስከበር ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
ሀገራዊ መግባባትን በመገንባት በሀሳብ የበላይነት፣ በሰላም የተመሠረተና የብልፅግና ርዕይ ያለው ሀገር መሻት ምላሽ ለመስጠት ጉባኤው ጠቃሚ ነው ያሉት ደግሞ ነብያት ስብሀቱ ናቸው።
አብነት ንጉሴ የተባሉት የመዲናዋ ነዋሪ በበኩላቸው፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የትውልድን የመመካከርና የመደማመጥ የአስተሳሰብ ባህል የሚያጎለብት የጋራ መድረክ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመደማመጥና በመመካከር ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችንና ቁርሾዎችን በሰለጠነና ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጉባኤው የሚያበረክተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
Exit mobile version