Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የባህር በር ባለቤትነት ለፖለቲካዊ ተፅእኖ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህር በር ባለቤትነት በዓለም አቀፍ ፖለቲካ እና ጂኦፖለቲካዊ ግንኙነት ውስጥ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም።
በታሪክ አጋጣሚዎች እንደተስተዋለው የባህር በር ባለቤት የሆኑ ሀገራት ከኢኮኖሚ እድገታቸው ባለፈ በአካባቢያቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ፣ የደህንነት እና የዲፕሎማሲያዊ ተጽእኖ የመፍጠር አቅም ይኖራቸዋል፡፡
የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለመድረስ በባህር ባለቤት ሀገራት ላይ ጥገኛ ይሆናሉ። ይህ ጥገኝነት የባህር በር ባለቤት የሆኑ ሀገራት በታሪፍ፣ በወደብ አገልግሎት ክፍያ እና በትራንዚት ህጎች በኩል በጎረቤቶቻቸው ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ተጽእኖ እንዲኖራቸው ያደርጋል።
የባህር መውጫ በር ያላቸው ሀገራት በችግር ጊዜ የውጭ ንግዳቸውን እና የነዳጅ አቅርቦታቸውን ያለ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ማስቀጠል ይችላሉ፤ ይህም የፖለቲካ ነጻነታቸውን ያጠናክራል።
የባህር በር ባለቤትነት ጠንካራ የባህር ኃይል ለመገንባት እና በአካባቢው የሚገኙ የባህር አካላትን ለመጠበቅ ያስችላል። ይህ አቅም ስጋቶችን ከሩቅ ለመግታት እና በክልላዊ የደህንነት ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ተሳታፊ ለመሆን ይረዳል።
እንደ ባብ ኤል-መንደብ፣ የሱዊዝ ካናል ወይም የሆርሙዝ ሰርጥ ባሉ ወሳኝ የባህር መስመሮች አቅራቢያ የሚገኙ ሀገራት ዓለም አቀፉን የንግድ እንቅስቃሴ በንቃት የመከታተልና የመቆጣጠር አቅም ስለሚያገኙ ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር ያላቸውን የመደራደር አቅም ከፍ ያደርጋል።
የባህር በር የሌላቸውን ሀገራት የንግድ መስመር በመፍቀድ ወይም በመከልከል ረገድ የሚደረጉ ስምምነቶች ብዙውን ጊዜ ከፖለቲካዊ እና ከደህንነት ትብብር ቅድመ-ሁኔታዎች ጋር ይያያዛሉ።
በቀጣናዊ የትብብር ማዕቀፎች ውስጥ የባህር በር ያላቸው ሀገራት የኢኮኖሚ እና የትራንስፖርት ትስስር ማዕከል በመሆናቸው የፖለቲካ ውሳኔዎችን ከራሳቸው ጥቅም ጋር ለመዋጀት አመቺ ይሆንላቸዋል።
በአጠቃላይ የባህር በር ያላቸው ሀገራት በንግድ፣ በደህንነት እና በዲፕሎማሲ መስክ ያሏቸው እድሎች በጎረቤቶቻቸው እና በዓለም አቀፍ አካላት ዘንድ ያላቸውን ፖለቲካዊ የመደራደር አቅም በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል።
ኢትዮጵያ የምታነሳውም ህጋዊና ፍትሃዊ የባህር በር ባለቤትነት መብት ጥያቄዋ፤ የድንበር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ የሀገር ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ነጻነት እና የጂኦፖለቲካዊ ተጽእኖ የማግኘት ነው።
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version