Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መንግሥት፣ የግል ባለሀብቱንና ሕዝቡን ባሳተፉ የልማት ሥራዎች ታላላቅ ስኬቶች ተመዝግበዋል

ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥና የሕዝቦቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል አዳዲስ ሀገር በቀል ፍልስፍናዎችንና የአሠራር ስልቶችን በመተግበር ላይ ትገኛለች።
ከእነዚህም መካከል ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የሚይዘው የመደመር ፍልስፍና ነው።
የመደመር መንግሥት ሀገራዊ ልማትን በባሕላዊው የመንግሥት በጀት ብቻ ከመደገፍ ወጥቶ፣ መንግሥትን፣ የግል ባለሀብቱንና መላውን ሕዝብ በአንድነት የሚያስተባብሩ አዳዲስ አሳታፊ የልማት ሞዴሎችን ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ይህ ሦስትዮሽ ቅንጅት ሀገሪቱ ለዘመናት የነበሩባትን ውስብስብ የልማትና የመሠረተ ልማት እጥረት ችግሮች በአጭር ጊዜና በጥራት ለመፍታት ያስቻለ ሲሆን÷ ለፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለከተሞችና ገጠሮች መዋቅራዊ ሽግግር መሠረት ጥሏል።
የመደመር ፍልስፍና ዋነኛ ማጠንጠኛ አቅምን፣ ዕውቀትንና ሃብትን በአንድ ላይ በማቀናጀት ከብክነት የጸዳና ፈጣን ውጤት የሚያስገኝ ሥራ መሥራት ነው።
ቀደም ሲል ለታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የሚሆን ፈንድ ለማግኘት በብድርና በእርዳታ ላይ የመንጠልጠል አባዜ የነበረ ሲሆን÷ አሁን ግን ይህ አስተሳሰብ በቁጭት ተቀይሮ በራስ አቅም ላይ መተማመንን ፈጥሯል።
መንግሥት ሃሳብ አመንጪነቱንና የመሪነቱን ሚና በመውሰድ ምቹ የፖሊሲ ከባቢዎችን ሲፈጥር፣ የግል ባለሀብቱ ደግሞ በገንዘብና በዕውቀት ድጋፍ በማድረግ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባለው (በዳያስፖራው) አማካኝነት የአንድ ወር ደመወዝ ከመለገስ ጀምሮ በጉልበትና በገንዘብ የታላላቅ ፕሮጀክቶች ባለቤት መሆን ተችሏል።
ለዚህም እንደ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ያሉ ሀገራዊ ንቅናቄዎች ዋነኛ ማሳያ ናቸው። እነዚህ መርሐ ግብሮች ኃብትን ከሕዝብና ከባለሃብቱ በፈቃደኝነት በማሰባሰብ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለቱሪዝምና ለከተማ ውበት ፕሮጀክቶች ግንባታ ውለዋል።
በመንግሥት፣ በግል ባለሀብትና በሕዝብ ትብብር የተገነቡና አሁንም በመገንባት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ አካታች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ ነው። የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለዚህ ስኬት ተጨባጭ ማሳያ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ የተጀመረውና በአሁኑ ወቅት ወደ ተለያዩ የክልል ዋና ዋና ከተሞች የተሻገረው የኮሪደር ልማት የመደመር መንግሥት ትልቅ አሻራ ነው። ይህ ፕሮጀክት ንፁህና አረንጓዴ የመንገድ ዳርቻዎችን፣ የሕዝብ መዝናኛ መናፈሻዎችንና ዘመናዊ የመሠረተ ልማት አውታሮችን በመገንባት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለውጭ ኢንቨስትመንትና ለቱሪስት ደግሞ ሳቢ አድርጓቸዋል።
በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ ወደ ገጠር አካባቢዎች በመስፋፋት ሞዴል የገጠር መንደሮችን በመገንባት የከተማና የገጠር የኑሮ ደረጃ ልዩነትን በማጥበብ ረገድ ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበ ይገኛል። በአጠቃላይ በኮሪደሩ ልማት የመንግሥት፣ የግል ባለሀብት እና የሕዝቡ ተሳትፎ የላቀ ነው፡፡
ሌላኛው የሦስቱ አካላት የቅንጅት ማሳያ የቱሪዝም መዳረሻዎችና ሎጂዎች ናቸው፡፡ በዚህም የገበታ ፕሮጀክቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በመሠረተ ልማት እጦት ምክንያት ሳይነኩና ተሸፍነው የቆዩ የተፈጥሮ መስህቦች አሁን ላይ ወደ ተወዳዳሪ የኢኮ ቱሪዝም ማዕከላትነት ተቀይረዋል።
ለማሳያም ጥቂቶቹን እናንሳ፡፡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተገነባው የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ፣ የሃላላ ኬላ ሎጅ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የወንጪ ኢኮ ሎጅ እንዲሁም በአማራ ክልል የሚገኘው የጎርጎራ ፕሮጀክት በተቀናጀ ርብርብ የተጠናቀቁ አስደናቂ ስኬቶች ናቸው።
እነዚህ ሎጆች ሀገራዊ አቅምን ከማሳየት ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩና የሀገሪቱን የቱሪዝም ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ የቀየሩ ናቸው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር መላውን የሀገሪቱን ዜጋ ከጫፍ ጫፍ በነቂስ ያንቀሳቀሰና የመደመር እሳቤን በተግባር የገለጠ ሆኗል፡፡ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለመገንባትና የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ መላው ሕዝብ በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ያሳየው የአረንጓዴ ዐሻራ ተሳትፎ ሌላኛው የመደመር ስኬት መገለጫ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የተጀመረው የጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ ንቅናቄም የሕዝብን ጤናና ንፅህና ለመጠበቅ ማኅበረሰቡንና ባለሃብቱን ያስተባበረ ቀጣይነት ያለው ስራ ነው።
በአጠቃላይ የመደመር መንግሥት ያስመዘገባቸው ታላላቅ ስኬቶች በእሳቤው መሠረት የተፈጸሙ፤ መንግሥት፣ የግል ባለሀብትና ሕዝብ ያስተባበሩ ናቸው፡፡
በመደመር እሳቤው ውስብስብና ሰፊ ጊዜ የሚወስዱ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሳይፎክሩ፣ በጥራትና በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ኢትዮጵያ በተግባር አሳይታለች።
ይህ የተቀናጀ የሥራ ባሕል የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ከማፋጠኑም በላይ፣ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ልማት ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸውና በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲያሳድጉ ረድቷቸዋል።
ይህንን የጋራ ርብርብ አጠናክሮ ማስቀጠል ሀገሪቱን ወደ ላቀ የብልጽግና ማማ እንደሚያደርሳት ጥርጥር የለውም።
Exit mobile version