አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በስምንቱ ቡድኖች ጸድቀው የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦችን የሚያጣጥምና ድግግሞሽን የሚያስተካክል ቡድን በዛሬው ዕለት ሥራ ይጀምራል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ሥላሴ የሀገራዊ ምክክሩን አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ እየሰጡ ነው፡፡
ኮሚሽነሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ እያንዳንዳቸው 500 አባላት ያሏቸው ስምንቱም ቡድኖች ስራቸውን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ቡድኖች የተስማሙባቸውን ምክረ ሀሳቦች የሚያጣጥም፣ የሚቃረኑ ጉዳዮችን የሚያስተካክልና ድግግሞሽ ያሉባቸውን ምክረ ሀሳቦች ወደ አንድ ለማምጣት የሚሰራ ቡድን ተቋቁሟል ነው ያሉት፡፡
ከእያንዳንዱ ቡድን ተመርጦ የተቋቋመው ቡድን ዛሬ ከሰዓት በኋላ ስራውን እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡
ቡድኑ የሚያከናውነው ስራ ምክረ ሀሳቦችን ወጥነት ባለው መንገድ አጠቃልሎ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ነው ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ የገለጹት፡፡

