Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስቀደመው የባሕር በር ዲፕሎማሲ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በታሪኳ ለረጅም ዘመናት የባሕር በር ባለቤትና የራሷን የባሕር ኃይል አደራጅታ ስትንቀሳቀስ የነበረች ታላቅ አፍሪካዊት ሀገር ነች፡፡

ነገር ግን በታሪካዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች ምክንያት ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የባሕር በር አልባ ሀገር ሆና ለመቆየት ተገድዳለች።

ይህ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብት መታጣቱ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በብሔራዊ ደኅንነትና በቀጣናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድር መቆየቱ የአደባባይ ምስጢር ነው።

ይሁን እንጂ የመደመር መንግሥት ይህንን የዲፕሎማሲ መሽኮርመም በመስበር፣ የሀገሪቱን የቀይ ባሕር ጥቅምና የመውጫ ፍላጎት በግልጽ ይፋ አድርጓል።

ይህ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ ተጨባጭና ተስፋ ሰጪ ፍሬዎችን ማፍራት ጀምሯል።

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ፍላጎት ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መድረኮች ላይ በግልጽ ከመነሳት ይልቅ በዝምታ ይታለፍ የነበረ ጉዳይ ነበር።

ይህ አካሄድ ሀገሪቱን የዲፕሎማሲ መሽኮርመም ውስጥ ከትቷት የነበረ ሲሆን፤ ጥቅሞቿንና መብቶቿን በግልጽ እንዳታስከብር አድርጓት ቆይቷል።

ይሁን እንጂ የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ታሪካዊ መብት፣ በዓለም አቀፍ ሕግ የተደገፈ የተሳትፎ ድርሻና የውኃ ላይ የመውጫ ፍላጎት በአደባባይና በግልጽ ማሳወቁ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

ይህ ግልጽነት ጎረቤት ሀገራትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ዘላቂ የህልውና ጥያቄ እንዲረዱና በጉዳዩ ላይ ይፋዊ ውይይትና ድርድር እንዲጀመር አስገድዷል።

የኢትዮጵያን ፍላጎት ልዩ የሚያደርገውና ለዲፕሎማሲው ስኬት መንገድ የጠረገው መርህ በሌሎች ላይ ጫና ከመፍጠር ይልቅ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው።

ይህ አካሄድ የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት ከቀጣናዊ የኢኮኖሚ፣ ከሕዝቦች ትስስርና ከዘላቂ ሰላም ጋር የሚያቆራኝ በመሆኑ፣ ለአካባቢው ሀገራትም አዲስ የልማት ዕድል የሚፈጥር ስትራቴጂ ሆኖ ተገኝቷል።

ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር መብቷንና የባሕር በር የመውጫ ፍላጎቷን በግልጽ በማሳወቅ የጋራ ተጠቃሚነት የዲፕሎማሲ አቅጣጫን እየተከተለች ነው፡፡

ይህም ሀገሪቱን ከዓመታት ዝምታ ያወጣ ስትራቴጂያዊ ርምጃ ሆኖ ተመዝግቧል።

የባሕር በር ለሀገሪቱ የረጅም ዘመን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የብሔራዊ ደኅንነት ዋስትና ከመሆኑም በላይ በምሥራቅ አፍሪካና በቀይ ባሕር ቀጣና ውስጥ ያላትን ተገቢ የጂኦፖለቲካዊ ድርሻ እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት መልሳ እንድታረጋግጥ ያስችላታል።

Exit mobile version