Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመከላከያ ሠራዊትን በሰው ሰራሽ አስተውሎት የማዘመን ሥራ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም የቴክኖሎጂ ምጥቀት እየተፋጠነ በመጣበት ዘመን የሀገራት የደህንነትና የመከላከያ አቅም ከባሕላዊ የወታደራዊ አሰራር ባለፈ በዕውቀት፣ በመረጃ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየተወሰነ ይገኛል።

በተለይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት በውሳኔ አሰጣጥ፣ በመረጃ ትንተና፣ በስልጠናና በሎጂስቲክስ ዘርፎች የሚኖረው ሚና እየጎለበተ መጥቷል።

በዓለም አቀፍ የወታደራዊ እንቅስቃሴ ውስጥም የሰው ሰራሽ አስተውሎት በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋሉ እና በጦር ሜዳ ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር ላይ ይገኛል።

ይህንን የቴክኖሎጂ ሽግግር በመከተል የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተደገፈ ዘመናዊ የመከላከያ አቅም ለመገንባት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ በተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ራሱን በማዘመን የማድረግ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ የሚገኘው የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት ከዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር ለማስማማት ከተወሰዱ ጠቃሚ ርምጃዎች መካከል አንዱ ነው።

ይህ ስምምነት በስልጠናና ትምህርት፣ በሎጂስቲክስ፣ በሳይበር ደህንነት፣ በወታደራዊ ጤና ጥበቃ፣ በአየር ኃይልና በኤሌክትሮኒክስ ውጊያ ዘርፎች ላይ በጋራ ስራ ለመስራት ያስችላል።

እንዲሁም የሠራዊቱን የሰው ኃይል ከማብቃት ጋር በተያያዘ የሲሙሌሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመከላከያ ሠራዊቱ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮሌጆችና የስልጠና ማዕከላት በሲሙሌተር ቴክኖሎጂ እንዲደራጁ ማድረግ የሰልጣኞችን ተግባራዊ ዝግጁነት ለማሳደግ ወሳኝነት አለው።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በስምምነቱ ወቅት÷ የሠራዊቱን ሁለንተናዊ አቅም በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባትና ተቋሙን ከወቅቱ የቴክኖሎጂ እድገት ጋር ለማስማማት በስሩ የሚገኙ የትምህርትና የማሰልጠኛ ተቋማት በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲታገዙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ኤአይ በሳይበር ኦፕሬሽንና በኢንተለጀንስ ዘርፍ ያለው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተለይም መረጃን በፍጥነት ማሰባሰብና መተንተን፣ የሳይበር ስጋቶችን መለየትና የመከላከል ዝግጁነትን ማሳደግ ከትብብሩ የሚጠበቁ ውጤቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በመሆኑም የሁለቱ ተቋማት ትብብር ቴክኖሎጂን ከመከላከያ ሥርዓት ጋር በማስተሳሰር የኢትዮጵያን የመረጃ፣ የሳይበር ደህንነት፣ የስልጠናና የሎጂስቲክስ አቅም ለማዘመን የሚያግዝ አዲስ የመከላከያ ቴክኖሎጂ ምዕራፍ እየከፈተ ሆኗል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version