Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አረንጓዴ ዐሻራ ዘላቂ ልማትን የሚያጠናክር ሀገራዊ ርምጃ መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የተፈጥሮ ሀብታችንን የመጠበቅ፣ የማልማትና የዘላቂ ልማታችንን መሠረት የማጠናከር ስትራቴጂያዊ ሀገራዊ ርምጃ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ይህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም አቅማችንን እያጠናከረ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የተፈጥሮ ሥነ ምህዳራችንን በማስተካከልና በማልማት ኢትዮጵያን አረንጓዴ ምድር እያደረጋት መሆኑን አውስተዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትም ኢትዮጵያ በራሷ አቅምና በዜጎቿ የጋራ ጥረት የተፈጥሮ ሀብቷን መጠበቅና ማልማት እንደምትችል ያረጋገጡና በአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ረገድ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ የሚሆኑ የወል ስኬቶች ናቸው ነው ያሉት።
የተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅ ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን፣ ለግብርና ምርታማነት፣ በምግብ ራስን ለመቻል እና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሠረት እንደሆነ አመልክተዋል።
ለዚህም ነው አረንጓዴ ዐሻራን የምግብና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን ለማጠናከር ዋነኛ ዘላቂ ሀገራዊ የልማት ትኩረታችን ያደረግነው ሲሉም አስረድተዋል።
ይህ ትውልድ የተፈጥሮ ሀብቱን በመጠበቅና በማልማት የዚህ ዘመን መሻቱን ከማሟላት ባለፈ ለመጪው ትውልድ የበለጸገችና የማትበገር ኢትዮጵያን የማስረከብ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራና አስተማማኝ መሰረት ለመጣል የተጀመሩ የተቀናጁ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
Exit mobile version