ኢትዮጵያ በሕገ ወጡ የህውሓት ቡድን የስልጣን ዘመናት ለሦስት አስርት ዓመታት በሙስና አሜከላ ስትወጋ፤ በሌብነት ማቅ ስትማቅቅ ቆይታለች፡፡
እኔ ብቻ ልብላ በሚል መርዝ የተተበተበው ህገወጡ ቡድን በስልጣን ላይ በዘለቀባቸው እነዚያ ዓመታት ሀገርና ሕዝብን ከቁብ ሳይቆጥር በስግብግብነት በኢትዮጵያ ምድር ላይ የዘረፍ፣ የስርዓታዊ ሌብነትና የኢኮኖሚ ምዝበራ ሲፈጽም ቆይቷል።
መንግሥታዊ መዋቅሩን እንደ ግል ንብረት በመጠቀም የሕዝብን ላብና እንባ በመመገብ የተገነባው ይህ አሰራር ሀገሪቱን የገደል አፋፍ ላይ ጥሏት የነበረበት ታሪክ አይዘነጋም፡፡
የእድገት ሞተር አንቀሳቃሽ የነበረው ኢንቨስትመንት በእነዚያ ስግብግብ መዳፎች ምዝበራና በሌብነት ተጠፍንጎ የሀገር የልብ ትርታ መዳከሙ አይዘነጋም፡፡
ለሀገር ዕድገት ወሳኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪም እውነተኛ ባለሀብቶችንና ሀገርን ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ በምስጢራዊ የጥቅም ሰንሰለት ከቡድኑ ጋር ለተመሳጠሩ ሕገ ወጦች ብቻ በመዳረጉ የኢኮኖሚ ነፃነትን የገደለ ከባድ አደጋ ሆኖ አልፏል።
በልማት ሽፋን በተዘረጋው የሙስና መረብ ሌብነቱ አቅሙን እያፈረጠመ መለያውን እየቀያየረ ቀጠለ፤ ይህ ሥርዓታዊ የሀብት ምዝበራ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ረገድ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏታል።
ከውጭ የሚገቡ ብድሮችና እርዳታዎች እንዲሁም የሀገር ውስጥ ግብር ለሕዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መዋል ሲገባቸው፤ ወደ ጥቂቶች ኪስና ከሀገር ውጭ ወደሚገኙ ምስጢራዊ የባንክ አካውንቶች ይጎርፉ ጀመር፡፡
በሕዝቡ ወዝ የተገኘ የሀገር ሀብት ጥቂቶችን ሲያወዛ፤ ኢትዮጵያዊው በገዛ ሀገሩ ባዳ በራሱ ሀብት ባይተዋር፤ ዕጣ ፈንታውም ድህነት፣ ስደትና የዕለት ጉርስ ፍለጋ ብቻ እንዲሆን ተገደደ።
እነዚያ የሌብነት ጥማት ያደረቃቸው ጉሮሮዎችም የታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ካዝና ለማራቆት ተኝተው አላደሩም፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የደም ስርና የትንሣኤ ማማ ሆኖ ሳለ፤ የሌብነት ጥማት ያልቆረጠላቸው የሕገ ወጡ ህወሓት መዳፎች ግን ዜጎች ከጉርሻቸው ቆርሰው ለሀገር ክብር የሰበሰቡትን አደራ መዝብረውታል፡፡
የግዙፍ ፕሮጀክት ውሎችን ልምድ ለሌላቸው ተቋራጮች በመስጠትና በጀት በማውደም የዕድገት ገናናውን ታሪክ በከፍተኛ መዘግየትና ብክነት አቁስለውታል።
ዛሬም ቢሆን በውጭ ኃይሎች ድጋፍ እየተመራ የጠላትን ፍላጎት ለማስፈጸም በእንብርክክ እያዘገመ ያለው ሕገ ወጥ ቡድን በማምሻ እድሜውም ቢሆን የሌብነትን ጫፍ መልቀቅ ጣር ሆኖበታል፡፡
“ሌባ ለአመሉ…” እንዲሉ ያገኘውን እያግበሰበሰ የታሪክ አሜከላ መሆኑን በግልፅ እያሳየ ይገኛል፡፡
በሔብሮን ዋልታው

