Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የባንዳና ባዕዳ ሴራ አስፈጻሚው ሕገ ወጡ ሕወሓት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል እልፍ ችግሮችንና መሰናክሎችን በልጆቿ ቆራጥነት፣ አንድነት እና ጀግንነት ተሻግራ ለትውልድ ቆይታለች፡፡

በእነዚህ የሺህ ዓመታት መልካምና አስቸጋሪ ጉዞዎቿ ውስጣዊ ችግሮችንና ከውጭ የተቃጡ ተግዳሮቶችን በድል ተሻግራ ዛሬ ላይ ደርሳች፡፡

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጣና፣ የነጻነት ታሪኳ እና የተፈጥሮ ሀብቷ ከውስጥም ከውጭም ያሉ ጠላቶቿ እንዳይተኙላት ምክንያት ሆነዋል፡፡

በየጊዜው የሚገጥሟት ፈተናዎች ጎን ለጎን በውጫዊ እና ተልዕኮ ተቀባይ በሆኑ ውስጣዊ ታሪካዊ ጠላቶቿ የሚጠነሰሱ ናቸው፡፡

ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት ትጠቀምበት ወደነበረው ቀይ ባሕር እንዳትመለስና እንዳትጠቀም ለማድረግ እየተፍጨረጨረች ሲሆን÷ ሌላኛዋ ታሪካዊ ጠላት ግብጽ ደግሞ በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ላይ ተቸንክራ “የዓባይ ወንዝ የኔ ብቻ ነው” በሚል አባዜ በሀገር ውስጥ ተላላኪ ባንዳዎች እገዛ እንቅፋት ስትፈጥር ኖራለች፡፡

ምንም እንኳን የዓባይ ወንዝ በልጆቿ ጽኑና ቆራጥ ርምጃ ፊቱን ወደ እናት ሀገሩ አዙሮ የልማት አለኝታ ቢሆንም፣ አሁንም ከተንኳሽ ድርጊቷ አላረፈችም፡፡

እዚህ ጋር በተያያዘ “ጽምዶ” የተሰኘው የባዕዳና የባንዳ ስብስብ ይነሳል፡፡ ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን እና ሌሎች ፅንፈኛ ቡድኖች በተልዕኮ ተቀባይነት፣ ኤርትራና ግብጽ ደግሞ ከጀርባ ሆነው ይዘውሩታል፡፡

ስልጣንን በኃይል ለመጨበጥና በጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት የሚነዱ ሌሎች አካላትን ለእኩይ ግባቸው በማስተባበር ሀገራዊ ተቋማትን፣ የህዝብና የታሪክ እሴቶችን የማናጋት ተልዕኮ በመቀበል እየተፍጨረጨሩ ነው።

ይህ ጥምረት የኢትዮጵያን ህዝብ ሰላም መንሳትና ከልማት የማደናቀፍ አልሞ እየሰራ ነው፡፡የቡድኑ ዓላማ በሺህ ዓመታት ደማቅ ታሪክ የተገነባችውን የኢትዮጵያን ሀገራዊ፣ ማህበራዊና ሰብዓዊ መሰረቶች በእኩይ ተልዕኮው ማደብዘዝ ነው።

ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህን እኩይ ጥምረት የተቀናጀ የሴራና የሐሰት መረጃዎች ተረድቶ ሀገሩን በጋራ መጠበቅ አለበት፡፡

በተባበረ አቅም የሀገሪቱን ትክክለኛ እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያስረዱ የዲፕሎማሲ እና የሕዝብ ግንኙነት ስልቶችን በመጠቀም የዚህን ቡድን አፍራሽ አጀንዳ ማክሸፍ ይገባል።

የሀገሪቱን ልማትና ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ማስቀጠል  የሚቻለው የባንዳዎችን እቅድ በማክሸፍ፣ የውስጥ አንድነትን በማጠናከር፣ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት በመፍታት እና ሕዝቡ ሀገራዊ ጥቅሙን ከቡድናዊ ፍላጎት አስበልጦ ሲቆም ብቻ ነው።

በመልካም ፈቃዱ

Exit mobile version