አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ የብሪክስ መድረኮች አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ተቋማት እውነተኛ ውክልና እንዲኖራቸው እየሞገተች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2023 በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ ጉባኤ አባል ሆና ከተጋበዘች ጀምሮ በ2024 በሩሲያ ካዛን ከተማ በተካሄደው 16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን አድርጋለች፡፡
በመቀጠልም በብሪክስ ወጣቶች መድረክ እንዲሁም በፀረ ሙስና እና በኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ በተዘጋጁ የማዕቀፉ የሚኒስትሮችና ባለሙያዎች ስብሰባዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡
የዓለም አቀፉ የሥልጣን፣ የውክልና እና የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅር በአዲስ የጂኦፖለቲካ እውነታ እየተፈተነ ባለበት ወቅት ታዲያ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ድምፅ የማጠናከር ጥረቷን በብሪክስ መድረክ ላይም እያስቀጠለች ነው።
በተለይም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የዓለምን የፀጥታና የሰላም ጉዳዮች በመወሰን ትልቅ ሥልጣን ያለው ተቋም ቢሆንም፤ አሁንም የአፍሪካ ቋሚ ውክልና አለመኖሩ የታሪካዊ ውክልና ክፍተት ሆኖ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ ይህንን ክፍተት ለመዝጋትና አግላይ የዓለም ስርዓትን ለማስተካከል እንደ ብሪክስ ባሉ መድረኮች ከአፍሪካ የጋራ አቋም ጎን በመቆም ላይ ትገኛለች፡፡
ለአብነትም በብራዚል ሪዮ ዲ ጄኔሮ በተካሄደው 17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በዓለም የፋይናንስ ሥርዓት ፍትሐዊነት እንዲሰፍንና አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖራት ጠይቃለች፡፡
በተጨማሪም የዕዳ እፎይታና የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ላይ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲደረግ እንዲሁም አፍሪካውያን አንድነታቸውን በማጠናከር አህጉሪቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሊያጋጥሟት የሚችሉ ፈተናዎችን መቋቋም እንደሚገባቸው አቋም ይዛለች፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የጋራ አቋም በማጠንከር፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካይነት እንዲሻሻል በመጠየቅና የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፍ የፀጥታ ውሳኔዎች ውስጥ እንዲጠናከር በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲና የአህጉራዊ ትብብር ታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ ያላት ሀገር ስትሆን፤ የአፍሪካ ነፃነት እና አንድነት እንዲረጋገጥና ጥቅሞቿ እንዲከበሩ የአንበሳውን ሚና ስትወጣ ቆይታለች፡፡
ይህም የፓን አፍሪካኒዝም መሪና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ መሪ ሀገርነቷን የበለጠ ያጠናክረዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

