አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክክርና መደመር እሴቶች የሚገነባው አሰባሳቢና ገዢ ትርክት የጸናች፣ የበለጸገችና የሁሉም እኩል ቤት የሆነች ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ ያስችላል፡፡
ጥንታዊ የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ የፖለቲካ ውጣ ውረዶችን ብታሳልፍም አሁንም ዘላቂ ሰላምና የጋራ የፖለቲካ መግባባት ያስፈልጋታል።
ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ደግሞ የሁሉም ማንነትና ፍላጎት የሚንጸባረቅበት አሰባሳቢ ትርክት መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ነጠላ ትርክት ለረጅም ዘመናት ለተከሰቱት የፖለቲካ ውጥረቶችና የመከፋፈል አመለካከቶች ዋነኛ መንስኤ ሆኖ ቆይቷል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ ያለፉ ስህተቶችን የሚያርምና የቀደሙ በጎ እሴቶችን የሚያከብር ሚዛናዊ አሰባሳቢ ትርክት መቅረጽ የጊዜው አስፈላጊ ጥያቄ ነው።
ለዚህ አሰባሳቢ ትርክት መፈጠር የመደመር እሳቤ ያለፈውን በጎ ታሪክ ጠብቆ የዛሬን አቅም በማቀናጀትና የነገን ብሩህ ተስፋ በማለም ቁልፍ ፍልስፍና ይሆናል።
ይህ የመደመር ጽንሰ ሐሳብ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት ውስጥ ኢትዮጵያዊነትና ሕብረ ብሔራዊነት እርስ በርስ የሚደጋገፉበትን አዎንታዊ መንገድ ያመላክታል።
በአሁኑ ወቅት በመገባደድ ላይ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ሒደት ደግሞ የእነዚህን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችና የፖለቲካ ኃይሎች ፍላጎት በሰለጠነ መንገድ ለማስተናገድ የተዘጋጀ ታሪካዊ መድረክ ነው።
በሀገራዊ ምክክሩ ወቅት በቅንነትና በግልጽነት የሚካሄዱ ውይይቶች ለወደፊቱ አሰባሳቢ ትርክትና ማህበራዊ ውል መሠረት የሚጥሉ ናቸው፡፡
ከዚህ አካታችና አሳታፊ የምክክር ሒደት የሚወጣው አሰባሳቢ ትርክት ሕዝባዊ ቅቡልነት አግኝቶ ደረጃ በደረጃ ወደ ማዕከላዊ “ገዢ ትርክት” ያድጋል።
እንዲህ ያለው ገዢ ትርክት መኖሩ የመንግሥታት መቀያየር የሀገረ መንግሥቱን መሠረታዊ ዓላማ ሳይነካ ሀገሪቱ በጽናትና በመረጋጋት እንድትቀጥል ያደርጋል።
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ገዢ ትርክቱ የሀገሪቱን ብዝሃነት፣ ቋንቋዎችና ባህሎች የሚያከብር ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ያካተተ መሆን አለበት።
ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ማለት የሁሉም ብሔሮች መብት ተከብሮ የጋራ ሀገር የሚገነባበት እይታ ነው፡፡ ይህም ጽንፈኝነትና አግላይነትን በማስወገድ ዜጎች ማንነታቸው ተከብሮ በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲኮሩ ያደርጋል።
ለዚህ ታላቅ ዓላማ ስኬትም መገናኛ ብዙሃን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻዎች አዎንታዊ እሴቶችንና ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን በማጠናከር የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ በምክክርና መደመር እሴቶች የሚገነባው አሰባሳቢና ገዢ ትርክት የጸናች፣ የበለጸገችና የሁሉም እኩል ቤት የሆነች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ያስችላል፡፡

