Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በግብርና ልማት ያላትን የአፍሪካ ምሳሌነት ይበልጥ አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ)  ኢትዮጵያ በግብርና ልማት ያላትን የአፍሪካ ምሳሌነት የበለጠ ለማጠናከር ከአህጉራዊ የግብርና ልማት ግቦች ጋር የተጣጣሙ እቅዶችንና ፕሮግራሞችን እየተገበረች መሆኑ ተገለጸ።

የኢጋድ ያዘጋጀው የ ሲኤኤዲፒ (CAADP) ግምገማ ሪፖርት አፈጻጸምና ተሞክሮ ልውውጥ ቀጣናዊ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ነው።

የግብርና ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪና የሲኤኤዲፒ የኢትዮጵያ ተወካይ ዜና ሃብተወልድ በዚህ ወቅት÷ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ የግብርና ልማት አጀንዳዎች ጋር የተጣጣሙ የ10 ዓመት የግብርና ልማትና ኢንቨስትመንት እቅዶችን አዘጋጅታ ስትተገብር መቆየቷን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአህጉሪቱ ሻምፒዮን እንደመሆኗ አሁንም ከሲኤኤዲፒ የካምፓላ ስምምነት ጋር የተጣጣመ የስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት በዘርፉ ያላትን ስኬት ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በየሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራና በኩታገጠም እርሻ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የአገሪቱን ተሞክሮ በአፍሪካ ደረጃ ለማጋራት ያስቻሉ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ የሰማያዊ ኢኮኖሚና ዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ በበኩላቸው÷ የአፍሪካ ግብርና ልማት ዋና ችግር የፖሊሲ እጥረት ሳይሆን የትግበራ ክፍተት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አህጉሪቱ አሁን ላይ ከማላቦ ስምምነት ወደ ካምፓላ ስምምነት ትግበራ በመሸጋገር ላይ መሆኗን ነው  ያመላከቱት፡፡

በፈረንጆቹ 2035 የአፍሪካን የግብርና ምርት በ45 በመቶ ማሳደግ፣ የአፍሪካ ውስጥ የግብርና ምርቶች ንግድን ሦስት እጥፍ ማሳደግና ቢያንስ 100 ቢሊየን ዶላር የህዝብና የግል መዋዕለ ንዋይ ማሰባሰብ ከካምፓላ ስምምነት ዋና ግቦች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢጋድ የግብርናና አካባቢ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዳሄር ኤልሚን በመወከል ንግግር ያደረጉት ሲልቪያ ሄንጋ (ዶ/ር)÷ በኢጋድ ቀጣና ከ60 ሚሊየን በላይ ሰዎች የምግብ ዋስትና እጦት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የምግብ እጥረቱን ለመቀነስ የተቀናጀ ሥርዓተ ምግብ፣ የተሻለ የመረጃ ሥርዓትና የጋራ ተጠያቂነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የሁለት ቀናት ውይይቱ የሲኤኤዲፒ 5ኛ ግምገማ ውጤቶችን በመገምገም ለካምፓላ ስምምነት ትግበራ የሚያግዙ ምክረ ሀሳቦችን ለማዘጋጀት፣ የአባል ሀገራትን ተሞክሮ ለመለዋወጥና በግብርና ልማት ዙሪያ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር እንደሚስችል ተመላክቷል።

 

Exit mobile version