አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ሻደይ፣አሸንድዬ፣ ሶለል እና ሌሎች ክብረ በዓላት ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴታቸው ተጠብቆ በድምቀት እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አለ የክልሉ ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ።
በቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበበ እምቢአለ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ በክልሉ በነሐሴ ወር የሚከበሩ የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና ሌሎች በዓላትን በልዩ ድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቋል።
የነሐሴ ወር ጸጋ የሆኑት ክብረ በዓላት “በዓል ድልድያችን፤ አንድነት መዳረሻችን” በሚል መሪ ሃሳብ በድምቀት እንደሚከበሩ ተናግረዋል።
በበዓላቱ አከባበር ሥነ ሥርዓት ላይ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ የሚመጡ እንግዶችን በልዩ መስተንግዶ ለመቀበል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።
የወጣት ሴቶች ክብረ በዓላት ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በሰሜን ወሎ አብዛኞቹ ወረዳዎች፣ በደቡብ እና ማዕከላዊ ጎንደር እንዲሁም በምዕራብ ጎንደር እና ምዕራብ ጎጃም ወረዳዎች በድምቀት እንደሚከበሩ አስረድተዋል።
በተጨማሪም የቡሄ በዓል ነሐሴ 13 ቀን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚከበር ሲሆን÷ በተለይም በደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር “ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር” በሚል ልዩ መርሐ ግብር እንደሚከበር ተናግረዋል።
እንዲሁም የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ ክብረ በዓላት በምሥራቅ ጎጃም እና በደብረ ማርቆስ አካባቢ በድምቀት እንደሚከበሩ ነው ያብራሩት።
በዓላቱ ሁለንተናዊ እሴታቸው ተጠብቆ አብሮነትና አንድነትን ባንጸባረቀ መልኩ በድምቀት እንዲከበሩ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ሳይንሳዊ ጥናቶች መጠናቀቃቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም ወልድያ፣ ደብረ ማርቆስ እና እንጅባራ ዩኒቨርሲቲዎች በዓላቱን በጥናትና ምርምር እየደገፉ ይገኛሉ ያሉት አቶ አበበ÷ጥናታዊ ጽሑፎቹ ለሕብረተሰቡ፣ ለወጣቱና ለምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ብለዋል፡፡
ለበዓላቱ ስኬት የሚመለከታቸው አካላት ሰፊ የሰላምና የቅንጅት ሥራዎች ማከናወናቸውን ገልጸው ÷ እንግዶች ሲመጡ የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች ለማቀላጠፍ የሆቴል ማህበራት፣ የአስጎብኚዎች እና የትራንስፖርት ማህበራት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
ጎብኚዎች በዓላቱን ከማክበራቸው ጎን ለጎን ታሪካዊ ቅርሶች እና የተለያዩ መዳረሻዎችን በመጎብኘት የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ

