Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሀገር ሉዓላዊነትና የቀጣናው የሰላም ዋስትና

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ሉዓላዊነት እና የሕዝቦችን ደህንነት ከማስጠበቅ ባሻገር፤ የቀጣናውና የመላው አፍሪካ አህጉር የሰላምና ደህንነት ዋስትና ሆኖ የዘለቀ ታላቅ ተቋም ነው።

በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ የሀገርን ህልውና ያስከበረው ይህ የጀግንነት ምሳሌ የሆነ ተቋም በሀገር ውስጥና በውጭ ኃይሎች የሚሰነዘሩ ትንኮሳዎችን በመመከት ረገድ የማይተካ ሚና ሲጫወት ቆይቷል።

የሰራዊቱ ጥንካሬና የቁርጠኝነት መንፈስ የሚመነጨው ከሕዝቡ ታሪካዊ የነጻነት ፍላጎትና ከኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስብጥር በተገነባው ሕዝባዊ መሰረቱ ነው።

“ክንደ ነበልባሉ” የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ዳር ድንበርና አየር ክልል ከማስከበር ባለፈ የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት የሚያረጋግጥ ጠንካራ መዋቅር ሆኖ ተገንብቷል።

በተጨማሪም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ የልማት አውታሮችን ከማንኛውም አይነት የውስጥና የውጭ ጥቃት በጽናት የመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ሰራዊቱ በሰው ኃይል ስልጠና፣ በዘመናዊ ወታደራዊ ትጥቅና በቴክኖሎጂ አቅሙ ላይ ከፍተኛ የለውጥና የዘመናዊነት ጉዞ በማድረግ ላይ ነው።

ተቋሙ ዘመናዊ  ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወይም ድሮኖችን፣ የውጊያ ጄቶችን እና የአየር ክልል ጥበቃ ቴክኖሎጂዎችን በማደራጀት የአየር ኃይል ብቃቱን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።

በተመሳሳይ መልኩ የተቀናጀ የባህር ኃይል መዋቅርን በመገንባትና ዘመናዊ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድመው የሚያክሽፉ የመረጃ ስልቶችን ስራ ላይ አውሏል።

የምድር ኃይሉም በዘመናዊ ከባድ መሳሪያዎች፣ በታንክ እና ሜካናይዝድ ክፍሎች እንዲሁም በላቀ የመረጃና የስለላ መዋቅር የበለጠ ተጠናክሯል።

ይህ የቴክኖሎጂና የትጥቅ ምጥቀት ሰራዊቱ በሀገር ውስጥ የሚነሱ የጽንፈኝነትና የህገወጥ ድርጊት ስጋቶችን በጽናት በመመከት የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር አስችሎታል።

ከሀገር ወሰን ተሻግሮም የአልሸባብን መሰል አሸባሪ ቡድኖች ስጋት በመቀነስ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፍተኛ ድርሻ ተጫውቷል።

በኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ባከናወናቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎችም ከፍተኛ የዲሲፕሊን እና የብቃት የበላይነቱን አስመስክሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተቀያየረ የመጣውን የጂኦፖለቲካ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሀገራችን በሰላምና በልማት ጎዳና እንድትራመድ የሚያስችል አስተማማኝ ቁመናን በመላበስ ከለላ ሆኖ ይቀጥላል።

Exit mobile version