አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ የሚያስችል ትልቅ ዕድል ነው አሉ ተመካካሪዎች፡፡
ተሳታፊዎቹ እንዳሉት ምክክሩ ለተሳታፊዎች ሀሳባቸውን በነጻነት የማቅረብ እድልን የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
ዓለምፀሐይ አሰፋ የተባሉት የምክክሩ ተሳታፊ በምክክሩ ውስጥ እያንዳንዱ ተሳታፊ ሀሳቡን በነጻነት ማንሸራሸሩን ገልጸው፤ የምክክሩ ሂደት ከታች አንስቶ በተደራጀ መልኩ የተለያዩ የተሳትፎ ሂደቶችን በማለፍ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ውሳኔ እንደሚወሰንና በተሳታፊዎች ላይ ተጽእኖ ይደረጋል በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጭ የነበሩ መረጃዎች ከእውነት የራቁ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ሌላኛው የምክክሩ ተሳታፊ ቹንኬድ ዴቪድ በበኩላቸው፣ በምክክሩ ሂደት ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲያቀርቡ ዕድል የሰጠ ሁነት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተነሱ ሀሳቦች ሀገራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ እና የበለጸገች ሀገርን ለትውልድ ለማስረከብ እንደሚረዳ ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ስር የሰደዱ ችግሮችን በውይይት መፍታት የሚያስችል ትልቅ ዕድል መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተሳታፊ አደም ሙሃመድ ናቸው፡፡
ችግሮችን በኃይል ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎች ኢትዮጵያን ጎድተዋት እንደነበረ ገልጸው፤ ምክክሩ ግን ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ዕድል ይሰጣል ብለዋል።

