Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢጋድ የቀጣናው ሀገራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አቀረበ

የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት በካምፓላ ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሐ ግብር ማዕቀፍ የምግብና እርሻ ሥርዓታቸውን በማዘመን የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢጋድ ያዘጋጀው የሲኤኤዲፒ (CAADP) ግምገማ ሪፖርት አፈጻጸምና ተሞክሮ ልውውጥ ቀጣናዊ ስብሰባ ማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ አቶ ዜና ሀብተወልድ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በተሞክሮ ልውውጥ መድረኩ የተገኙ ውጤቶች ወደ ተጨባጭ ብሔራዊ ፖሊሲዎች፣ ኢንቨስትመንቶችና የተግባር ርምጃዎች መተርጎም እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የመስኖ ስንዴ ልማት እና በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ጨምሮ የእርሻ ልማት ጥረቷን ከካምፓላ ዲክላሬሽን ጋር በማጣጣም እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ቀደም ሲል ካሏት የግብርና ልማት ዕቅዶች ልምድ በመነሳት ከካምፓላ ዲክላሬሽን ጋር የሚጣጣም አዲስ የ10 ዓመት የኢንቨስትመንት ማዕቀፍ እያዘጋጀች ነው ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ የሰማያዊ ኢኮኖሚና ዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ በበኩላቸው÷ የአፍሪካ የግብርና ትራንስፎርሜሽን የዘገየው ከፖሊሲ እጥረት ይልቅ ከተግባራዊነት ድክመት የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራት ምርታማነትን ሊያሳድጉ በሚችሉ እንደ የአፈር ካርታ ዝግጅት፣ የተሻሻለ የማዳበሪያ አጠቃቀም እና የሀገር ውስጥ የማዳበሪያ ምርት አቅምን ማጠናከር ባሉ ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል።

የካምፓላ ዲክላሬሽን የግብርና-ምግብ ምርትን በ45 በመቶ ለማሳደግ እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረገውን የግብርና ንግድ በሦስት እጥፍ ለማሳደግ አልሞ የተዘጋጀ ነው።

የኢጋድ ተወካይ ዶክተር ሲልቪያ ሄንጋ÷ ወደ ሰፊው የምግብ ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር የራብና ድህነትን ለመቀነስ መሰረት የሆነውን የምግብ ምርት ማሳደግን ሊጎዳው እንደማይገባ ተናግረዋል።

በአርሶ አደሮች ስልጠና እና በአካባቢ ጥበቃ ቴክኖሎጂዎች ማህበረሰብ አቀፍ ተቀባይነት ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንዲደረግም ጠይቀዋል።

ዶ/ር ሄንጋ ሀገራት የግብርና ንግድን ከማስፋፋታቸው በፊት ከምርት በኋላ በሚከሰቱ ብክነቶች፣ የማከማቻ፣ የትራንስፖርት እና የእሴት ጨመራ ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል።

ትርፍ ምርት የሚያመርቱ ሀገራት በኢጋድ ቀጣና ውስጥ የምግብ እጥረት ካለባቸው ገበያዎች ጋር በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና በኩል የተሻለ ትስስር ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

Exit mobile version