Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 4ኛው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 4ኛው የበለስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በዛሬው ዕለት ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።
የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ ማዕከሉን በመረቁበት ወቅት እንዳሉት፥ መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በማሻሻል የዜጎችን እንግልት የሚያስቀር ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው።
‎የበለስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ አራተኛው ማዕከል መሆኑን ገልጸው፤ የቤጉ መሶብ፣ የአሶሳ እና የባምባሲ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ቀደም ሲል ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰዋል።
በክልሉ በተዘረጋው ዘመናዊ የአገልግሎት ስርዓት እስካሁን በ124 የአገልግሎት ዘርፎች ከ53 ሺህ 900 በላይ ዜጎች የዲጂታል አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የእርካታ ደረጃውን 99 ነጥብ 2 ከመቶ ማድረስ ተችሏል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
የመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በቴክኖሎጂ በሥርዓት ወደሚመራ ተቋማዊ ብቃት ለመሸጋገር መሶብ አንዱ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
Exit mobile version