Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መሶብ፣ ከአገልግሎት ባሻገር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መሶብ ዘመኑን የዋጀና የተለያየ አገልግሎትን በአንድ ጣሪያ ሥር በመስጠቱ አሁን ላይ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት ቀላል ሆኗል።
ከዚህ ቀደም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ደጅ መጥናት፣ ከአንዱ ቢሮ ወደ ሌላው መንከራተት እንዲሁም በየደረጃው ባሉ የቢሮክራሲ ሰንሰለቶች ውስጥ መዋልና ማደር ለዜጎች አገልግሎት ለማግኘት ትልቅ ፈተና ሆነው ቆይተዋል።
ይህ አዝጋሚ የአገልግሎት አሰጣጥ በኢኮኖሚው ላይም ቀላል የማይባል ጫና ያሳድር ነበር፤ እንደ ንግድ ፈቃድ አሰጣጥ፣ የመሬት ምዝገባና የግብር አገልግሎት ያሉ ጉዳዮች መጓተት የግብይት ወጪን ከፍ ከማድረግ ባለፈ የኢንቨስትመንት ፍላጎትን ይቀንሳል፣ ሙስናንም ያባብሳል።
የዓለም ባንክ የአስተዳደር ጠቋሚዎች እንደሚያሳዩት ደካማ ተቋማዊ አቅም ያለባቸው ሀገራት የውጭ ኢንቨስትመንት ስበታቸው ዝቅተኛ ይሆናል፤ የግሉ ዘርፍ ልማት ይገታል፤ የመንግሥት ገቢ አሰባሰብም ይዳከማል፤ በዚህም የኢኮኖሚ ዕድገት ፍጥነት ይቀንሳል።
ከኢኮኖሚው ጫና ባሻገር፣ አንድን ቀላል ጉዳይ ለማስፈጸም የነበረው እንግልት የብዙዎችን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጪ በከንቱ ሲያባክን ኖሯል።
ይህ የተጓተተ አሰራር ለሌብነትና ብልሹ አሰራር ክፍተት የፈጠረ፣ ደላሎች መንግሥታዊ አገልግሎቶች ላይ እጃቸውን እንዲያስገቡ ያደረገ፣ የሰነድ መሰወርንና የሕዝብ ምሬትን ያባዛ ክስተት ነበር።
ሥር የሰደደ ችግሩን በዘመናዊ አሰራር ለመቅረፍ የመደመር መንግሥት የዘረጋው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የብዙዎችን እንግልት ያስቀረ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ባህልን በከፍተኛ ደረጃ የቀየረ የሪፎርም ፍሬ ሆኖ ብቅ ብሏል።
ዋና ዓላማውም የዜጎችን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ የተቀላጠፈ መንግሥታዊ አገልግሎት መስጠት ነው።
ቀደም ሲል ሳምንታትን አልፎም ወራትን ይወስዱ የነበሩ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች፣ ዛሬ በአንድ ጣሪያ ሥር በተሳለጠና በተቀናጀ መንገድ እየተሰጡ ናቸው።
ወደ ማዕከላቱ መድረስ ለማይችሉ ተገልጋዮችም፣ በተንቀሳቃሽ የመሶብ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበት አማራጭ ተመቻችቷል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እንደሚናገሩት፣ ጊዜና ጉልበት መቆጠቡ በዜጎች ኢኮኖሚያዊና ሥነ-ልቦናዊ ሕይወት ላይ ያሳደረው አዎንታዊ ተጽዕኖ ቀላል የሚገመት አይደለም። መጓተትና እንግልት ሲቀንስ፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነትና እርካታም በዚያው ልክ ያድጋል።
ዲጂታል ቴክኖሎጂን ከሰው ኃይል ብቃት ጋር በማጣመር የተዘረጋው ይህ አሰራር፣ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን ፀረ ሌብነት ዘመቻ የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ፣ የአስተዳደር ወጪንና ጊዜን በመቀነስ፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በማጠናከር፣ የመንግሥት ገቢ አሰባሰብን በማቀላጠፍ እና የኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻል ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
አገልግሎት ፈላጊው የሕብረተሰብ ክፍል ያለ ምንም እንግልትና አላስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች መብቱ ተከብሮ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻሉ፣ የመደመር መንግሥትን የሪፎርም ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠ አሰራር ነው።
በእመቤት ሲሳይ
Exit mobile version