Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠንካራ መሰረት የተጣለበት የትምህርት ዘርፍ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንዲት ሀገር በእውቀትና በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል መፍጠር ካልተቻለ በመሠረተ ልማት ሥራዎችና በካፒታል ብቻ ሁለንተናዊ እድገትን ማረጋገጥ የሚታሰብ አይደለም፡፡

ሀገራት የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዲችሉ እውቀትን ወደ ምርታማነት የሚቀይር ብቁ የሰው ኃይል ያሻቸዋል፤ ይህን የሰው ኃይል ለማፍራት ደግሞ ትምህርት የማይተካ ሚና አለው፡፡

የመደመር መንግሥት በትምህርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት በሀገር የወደፊት አቅም ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት መሆኑን በውል በመገንዘብ፥ የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት ስብራት ለመሻር ሰፊ የማሻሻያ ስራዎችን በትኩረት ሲከውን ቆይቷል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ተደራሽነትን፣ ጥራትንና ፈጠራን ያማከሉ አጠቃላይ ማሻሻያዎች ተተግብረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ በትምህርት ዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የሀገሪቱን የወደፊት ህልውና ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።

በዚህም በትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ ከባቢ ለመፍጠር ደረጃቸውን የጠበቁ የቅድመ አንደኛ፣ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ግንባታና የእድሳት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ሪፎርሙን ተከትሎ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ከ35 ሺህ በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመላ ሀገሪቱ በመገንባት ከ5 ሚሊየን በላይ ህጻናት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ተደርጓል።

በዚህ ረገድ በሕዝብና በባለሀብቶች ድጋፍ የሞዴልና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከናወነ ሲሆን፥ የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት 35 ሞዴል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አስገንብቷል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የኩረጃ አሰራርን ለማስቀረት ጥብቅ የፈተና ስርዓት ማሻሻያ ተተግብሮ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል።

በ12ኛ ክፍል ፈተና ከኩረጃና ከስርቆት ነጻ እንዲሆን በ2016 ዓ.ም የተጀመረውን የበይነ መረብ ፈተና ተደራሽነት በ2018 የትምህርት ዘመን ከ62 በመቶ በላይ ማድረስ የተቻለ ሲሆን፤ በቀጣይ ዓመት 100 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በመደመር መንግሥስት እየተተገበሩ ካሉ ሰው ተኮር ሥራዎች መካከል የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

በዚህም በተጠናቀቀው የ2018 የትምህርት ዘመን ከ8 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ከቅድመ አንደኛ እስከ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ተማሪዎች የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት በኩል የዩኒቨርስቲ አስተዳደር ቦርድና አመራሮች በብቃትና በውድድር ላይ ተመስርተው እንዲመረጡና እንዲመደቡ የሚያስችል ስርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ እንዲሆኑ በተጀመረው አሰራር መሰረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሽግግሩን የጀመረ ሲሆን፤ በዚሁ ተሞክሮ መነሻነት ዘጠኝ ዩኒቨርስቲዎች በቀጣይ ወደ ራስገዝነት ለመሸጋገር በሚያስችል ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡

በተለይም የትምህርት ስርዓቱን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ሲሆን፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ስራ ሲጀምር ለሀገሪቱ የቴክኖሎጂ አቅም አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው፡፡

የዲጂታል ትምህርትን ማስፋፋት፣ የብሔራዊ ፈተናዎችን ማዘመን፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠናና በከፍተኛ ትምህርት መካከል ያለውን ቅንጅት ማጠናከር በሪፎርሙ እየተተገበሩ የሚገኙ ተግባራት ናቸው፡፡

በተጨማሪም የመምህራንን ሙያዊ ብቃትና ማበረታቻ ማሻሻል እንዲሁም የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆችንና ዩኒቨርሲቲዎችን በማጠናከር ረገድ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

የመደመር መንግሥት እያከናወናቸው የሚገኙት እነዚህ ጥረቶችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች በትምህርት ስርዓቱ ክህሎት እንዲጎለብት ያደረጉ ሲሆን፤ የተማረና የነገዋን ኢትዮጵያ መረከብ የሚችል ጠንካራ ትውልድ ለመገንባት ጠንካራ መሠረት ጥሏል።

በቴዎድሮስ ሳህለ

Exit mobile version