Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የወላይታ ሕዝብ ለዓለም ያበረከተው ድንቅ ስጦታ “ጊፋታ”

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች ካስመዘገበቻቸው አንዱ የወላይታ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የሆነው “ጊፋታ” ነው።

ጊፋታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ስነ ልቦናዊ እሴቶችን አጣምሮ የያዘ የወላይታ ሕዝብ ለዓለም ያበረከተው ድንቅ የሰላምና የፍቅር መግለጫ ነው።የማህበረሰቡን ማንነት፣ አብሮነትና ወግ አስጠብቆ ያቆየ ታላቅ ባህላዊና ሕዝባዊ በዓል ነው።

«ጊፋታ» የሚለው ቃል «ታላቅ» (ባይራ)፣ «የመጀመሪያ» ወይም «መሻገር» የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን÷ ከአሮጌው ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን ያመላክታል።

ጊፋታ የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ፍጥረት በሙሉ፣ አእዋፋትና የቤት እንስሳት ጭምር በአንድነት የሚደሰቱበት፣ የአዲስ ሕይወትና የተስፋ ጅማሮ ተደርጎ በብሔረሰቡ ዘንድ ይታመናል።

የጊፋታ በዓል ሁለንተናዊ ፋይዳዎች

ጊፋታ የእርቅና የሰላም ምልክት ነው። በዓሉ የሚከበርበት ዋነኛው እሴት ሰላምና መታረቅ ነው። በዓመቱ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ተጣልተው የቆዩ ወገኖች፣ ተፋትተው የነበሩ ባልና ሚስቶች በጊፋታ ወቅት ይቅር ተባብለው ይታረቃሉ።

የሕዝቦች አንድነትና አብሮነት፣

ከሰኔ ወር (ጉሊያ ጎሼታ) ጀምሮ እስከ ጥቅምት ወር (ጎሏዋ እጌታ) ድረስ ባሉት ጊዜያት ማህበረሰቡ ስራዎችን በጋራ ያከናውናል፤ ይደጋገፋል።

በዓሉም በወላይታ ብሔረሰብ ብቻ ሳይሆን ከአጎራባችና ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በጋራ የሚከበር በመሆኑ ሀገራዊ ወንድማማችነትን ያጠናክራል።

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር፣

በዓሉ እርስ በርስ ስጦታ በመለዋወጥ፣ አብሮ በመመገብና የኢኮኖሚ ችግሮችን በጋራ በመወጣት የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባህልን ያጎለብታል።

ዘንድሮም ይህ ታላቅ ባሕላዊ ቅርስ የፊታችን መስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።

በማቴዎስ ፈለቀ

Exit mobile version