አዲስ አበባ፣ ነሐሴ14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እነሆ ጨለማ ተገፍቷል፤ ጉሙ ተበትኗል። የተሻለች፣ የተረጋጋችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማውረስ፣ በዚህ ትውልድ እጅ የፀና የተስፋ ቀንዲል ተለኩሷል፤ ስሙም ምክክር ነው።
ከግጭት የተላቀቀች እና ሠላሟን ያፀናች ኢትዮጵያን የሚያወርስ ድንቅ መድረክ መካሄድ ከጀመረ እነሆ አንድ ወር አልፎታታል።
የኢትዮጵያ ልጆች ለዘላቂ ሠላም፣ ልማት እና ዲሞክራሲ መረጋገጥ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠዋል።
የአሁኑ ትውልድ “ሀገሬ የግጭት ትውስታ የምታስወርስ ሳትሆን፣ ሰላምን፣ ዴሞክራሲን፣ ፍትሕን፣ መተማመንን፣ ልማትን እና ብልጽግናን ለነገ ልጆቿ ማውርስ አለባት” ብሎ ታሪካዊው ውሳኔውን በምክክሩ እያስተላለፈው ነው።
የኢትዮጵያ ልጆች በመከባበር እና በመደማመጥ በቁርጠኝነት የሚያደርጉት ውይይት ነገን ፍሬያማ እንደሚያደርግ ትልቅ ተስፋን ተጥሎበታል።
በውይይቱ ምክንያት ዘላቂ ሰላም ሲሰፍን በግጭት አዙሪት የሚባክነው ጊዜ እና ገንዘብ ወደ ማህበራዊ ልማት እንዲሁም ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ይውላል።
በዚህም ሀገሪቱ ወደ ዕድገት እና ብልፅግና ፈጥና ትደርሳለች።
ለዚህም ነው ምክክሩ የኢትዮጵያን ከፍታ እና ብልፅግናዋን ለሚሹ ሁሉ ትልቅ ተስፋን በማሰነቅ ዕድገቷን ለማይሹ የሀዘን ካባን ያለበሳቸው።
ባዕዳ እና ባንዳ ግንባር ፈጥረው የኢትዮጵያን ከፍታ አምርረው ቢቃወሙት ክፉ ምኞታቸው ከሽፎ፣ እነሆ ኢትዮጵያ ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና ጎዳና የሚያደርሳትን ጉዞዋን ቀጥላለች።
የሀገራዊ ምክክር ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገ/ሥላሴ እንደተናገሩት÷ በየትም ዓለም የሚደረጉ ሀገራዊ ምክክሮች መቶ በመቶ በሁሉ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ አይባልም።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው ምክክር በአብዛኛው ጉዳዮች ስምምነት ላይ የተደረሰበትና ለንግግርና ውይይት በር የከፈተ ነው ብለዋል። ይህም ለነገ ፅኑ መሰረት የሚጥል ነው፡፡
ይህ ጉዞ መዳረሻው ዘላቂ ሰላም፣ ጠንካራ ማኀበራዊ መስተጋብር እና ሀገራዊ መግባባት ነው። ችግሮች መፍትሄያቸው በምክክር ብቻ መሆኑን በማመን ልዩነቶችን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ማምጣታቸው የሀገርን ተስፋ አለምልሞታል።
ሀገራዊ ምክክሩ የትውልድን መፃኢ ዕድል የሚወስን ነው። ለዘመናት የተጠራቀመ አለመግባባቶችን እና ግጭትን የኢትዮጵያዊያን አንድነትና አብሮነት የሚያፀና ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
በሠራዊት ሸሎ
የግጭትን አዙሪትን የሚሽር የሠላም ቀንዲል …ምክክር

