Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ የፍራፍሬ ምርትና የውጭ ገበያ

default

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የፍራፍሬ ምርትን ከራስ ፍጆታ ባለፈ ወደ ውጭ በመላክ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የሚችል ምቹ የአየር ንብረት፣ ሰፊ የሚለማ መሬትና የውሃ ሀብት ያላት ሀገር ናት፡፡
በተለይም አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ እና ሲትረስ ዋና የፍራፍሬ ምርቶች ናቸው።
ባለፉት ስምንት ዓመታት በዘላቂነት ሲተገበር የቆየው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ካበረከተው አስተዋጽኦ ባሻገር ለምግብ ዋስትና እና ለውጭ ምንዛሪ ገቢ ያስገኘው ውጤት ፍሬያማ ሆኗል።
መርሐ ግብሩ እንደ አቮካዶ ያሉ የፍራፍሬ ተክሎች በበቂ ርጥበትና በጥሩ ሁኔታ እንዲያድጉ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛዋ ትልቋ የአቮካዶ ላኪ ሀገር መሆኗ ያላትን የግብርና እምቅ አቅም በግልጽ የሚያሳይ ነው።
የአቮካዶ ምርትን ለማሳደግ የተጀመሩ የችግኝ ተከላ፣ የተሻሻለ ዘር፣ የመስኖ ልማትና የጥራት ማሻሻያ ሥራዎች የዘርፉን አቅም እያሳደጉ ይገኛሉ።
ከችግኝ ተከላ ባለፈ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲስፋፋ አድርገዋል።
ባለፉት ዓመታት የፍራፍሬ ልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ከፍተኛ ስራ ተጨማሪ የወጪ ንግድ ምርቶች ሆነዋል፤ ዘርፉም ለውጭ ምንዛሪ ገቢ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ከሆርቲካልቸር ወጪ ንግድ ከተገኘው አጠቃላይ 490 ሚሊየን ዶላር ገቢ ውስጥ 21 ሚሊየን ዶላር ያህሉ ከፍራፍሬ ምርቶች የተገኘ ነው፡፡
በተጨማሪም ፍራፍሬን በጥሬው ብቻ ከመላክ ይልቅ ወደ ጭማቂ፣ ዘይት፣ የደረቀ ፍራፍሬ እና ሌሎች የተጨማሪ እሴት ምርቶች በመቀየር የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓና በአፍሪካ ገበያዎች በፍራፍሬ ምርት ተወዳዳሪ ለመሆን ከአቅርቦት ባሻገር ጥራትን ማሳደግ ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡
ይህ ውጤት የፍራፍሬ ወጪ ንግድ አሁንም ትልቅ የማደግ አቅም እንዳለው የሚያሳይ ሲሆን፤ የተጀመሩ የፍራፍሬ ልማት ሥራዎችን በቀጣይ በላቀ ትኩረት ማስቀጠል ይገባል፡፡
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version