አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2026/27 የውድድር ዓመት ነገ ምሽት ሻምፒዮኑ አርሰናል አዲስ አዳጊውን ኮቨንተሪ ሲቲን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጀምራል፡፡
በሊጉ በአዲሱ የውድድር ዓመት የሚተገበሩ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ቦርድ አዳዲስ የጨዋታ እና የዳኝነት ህጎች ይፋ ተደርገዋል፡፡
በዚህም መሰረት በጨዋታ መሃል ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ የሚወጣ ተጫዋች ቢያንስ ለአንድ ደቂቃ ያህል ከሜዳ ውጪ ሆኖ ይቆያል፤ ከዚህ ቀደም 30 ሰከንድ ነበር ይታወሳል፡፡
አንድ ቡድን የእጅ ውርወራ በሚያገኝበት ወቅት ዳኛው በሚያስጀምው የ5 ሰከንድ ጊዜ ውስጥ ኳስ ካልተወረወረ፤ የእጅ ውርወራው ለተቃራኒ ቡድን ይሰጣል፡፡
በተመሳሳይ በመልስ ምት ወቅት ዳኛው በሚያስጀምው 5 ሰከንድ ውስጥ ጨዋታው ካልተጀመረ ለተቃራኒ ቡድን የማዕዘን ምት ይሰጣል፡፡
በተጫዋቾች ቅያሪ ወቅት ተቀይሮ የሚወጣው ተጫዋች ከ10 ሰከንድ በላይ ከፈጀ፤ ተቀይሮ የሚገባው ተጫዋች ቢያንስ ለ1 ደቂቃ እንዲዘገይ ይደረጋል፡፡
ከአንድ ዲቂቃ በኋላ ጨዋታ የሚቋረጥበት እድል ሲፈጠር ወደ ሜዳ እስከሚገባ ድረስ ቡድኑ በጎዶሎ ይጫወታል፡፡
የቪዲዮ ረዳት ዳኞች (ቫር) አንድ ተጫዋች ሁለተኛ ቢጫ ካርድ በሚመለከትበት ወቅት የሁለተኛው ቢጫ ውሳኔ ግልጽ ስህተት ነው ብለው ካመኑ ዳኛው የቪዲዮ ረዳት ዳኝነትን ሊጠቀም ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ግብ ጠባቂዎች ጉዳት አስተናግደው ጨዋታ በሚቋረጥበት ወቅት አዲስ የጨዋታ ህግ በሙከራ ደረጃ እንደሚተገበር ተገልጿል።
ግብ ጠባቂ ጉዳት ሲያስተናግድ የክለቡ አሰልጣኝ አንድ ሌላ ተጫዋች ከሜዳ እንዲወጣ መምረጥ ይጠበቅባቸዋል።
ከሜዳ እንዲወጣ የሚደረገው ተጫዋች ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ ቢያንስ ለ1 ደቂቃ ከሜዳ ውጭ መቆየት አለበት።
በሃይለማርያም ተገኝ

