Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

4 ሺህ 233 አምራች ኢንዱስትሪዎች በ2018 በጀት ዓመት ወደ ስራ ገብተዋል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት 4 ሺህ 233 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ገብተዋል አሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ግምገማ እያካሄደ ይገኛል።

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተሰራው ስራ 5 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ማዳን ተችሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ 4 ሺህ 233 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህም ውስጥ 165 የሚሆኑት ከፍተኛ አምራቾች መሆናቸውን ነው የገለጹት።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በነበረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 57 ቢሊየን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩንም ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 69 ነጥብ 3 በመቶ የደረሰውን የማምረት አቅም በማሳደግ በ2019 በጀት ዓመት ወደ 74 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የአምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ውጭ ከሚልኳቸው ምርቶች 1 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት እንዲሁም ለ480 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የመደመር መንግሥት በሀገር ውስጥ የዘይት አምራቾች የነበራቸውን የገበያ ድርሻ ከ5 ወደ 18 ነጥብ 3 በመቶ ከፍ እንዲል ማስቻሉን ጠቅሰው፥ በ2019 በጀት ዓመት የዘይት ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በኤፍሬም ምትኩ

Exit mobile version