Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሶላር ኃይል አቅርቦት ባላቸው አካባቢዎች ነጻ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ አገልግሎት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጸሃይ ኃይል (ሶላር) አቅርቦት ባላቸው አካባቢዎች ለአዲስ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ነፃ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ ነፃ የቆጣሪ አገልግሎት የተጀመረው ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ ርቀው በሚገኙና የሶላር አማራጭ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ባላቸው አካባቢዎች ነው፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ለሚገኙ አዲስ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ነፃ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እንዲገጠም አዲስ አሠራር መጀመሩን ጠቁመዋል።
አዲሱ አሠራር በተለይም ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ ርቀው በሚገኙ የገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በቀላሉ እንዲያገኙ እና የኢኮኖሚ አቅማቸው የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነታቸውን እንዳይገድብ ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ ነው ብለዋል።
አሰራሩ በቅርቡ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ከሰኔ 2018 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት ብቻ 3 ሺህ 364 ደንበኞች ነፃ ቆጣሪ እንዲጠቀሙ ተደርጓል ነው ያሉት።
አዲሱ አሠራር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በኢኮኖሚ አቅማቸው ምክንያት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዳይርቁ ለማድረግና ንጹህ ኃይልን በማስፋፋት የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል የሚያግዝ ነው።
በሌላ በኩል አገልግሎቱ ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ ርቀው የሚገኙ የገጠር ከተሞችንና ማኅበረሰቦችን በሶላር ኃይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በጀት ዓመቱ ከዋናው ግሪድ ርቀው የሚገኙ 26 የገጠር ቀበሌዎችና ከተሞች በሶላር ኃይል አማራጭ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል።
አገልግሎቱ 54 የሶላር ኃይል ማመንጫዎችን በመገንባት ከ11 ሺህ በላይ አባወራዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
Exit mobile version