አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ትናንትም ዛሬም ከምክንያታዊነት የተፋታ፣ በሃይልና በአፈሙዝ ፍላጎትን ለመጫን የሚደረግ ጥረት ስትፈተን ኖራለች፤ ይህ ሀሳብ አልቦነት ይባላል።
የሰው ልጅ ሃይል፣ ክብርና ሀብትን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ከሀሳብ ተጣልቶ በጉልበት ብቻ ሁሉንም ለመጠቅለል መሞከር ነው መገለጫው፤ ከሀገር ይልቅ ሆድን ማስቀደም፤ ስልጣንን በኢመደበኛ መንገድ የመቆጣጠር ፍላጎትም ውጤቱ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው ይህንን እንደ ሀገራዊ ፈተና ፈርጀውታል፤ «ሐሳብ አልቦ ፖለቲካ የስራ ባህልን ያዳክማል፣ መሞዳሞድና ማስመሰልን ያበረታታል፣ የሀብት ማግኛ መንገድን በትውውቅና በጥቅም ትስስር ብቻ ያደርገዋል» ይላሉ።
በኢትዮጵያ ታሪክ ሀሳብ ዐልቦነት ደጋግሞ ተስተውሏል። የመሬት ላራሹንና ሌሎች አንገብጋቢ የፖለቲካ ጥያቄዎችን አንግቦ የተነሳው ያ ትውልድ በዚሁ ደዌ ምት ደርሶበት ቆይቷል፤ «የእኔ ብቻ ልክ ነው» በሚል ስሌት ጓዶቻቸውን የገደሉ ነበሩ፡፡
ዛሬም ድረስ «ሀሳባችሁን አምጡ እንመካከር» ሲባሉ «እንዋጋ» የሚሉ ፖለቲከኞች ብዙዎች ናቸው።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ሳሙኤል ሀንቲንግተን በ«Political Order in Changing Societies» ጽሑፋቸው እንደሚያብራሩት፣ ፈጣን ማህበራዊ ለውጥ ጥያቄ ይዞ ሲመጣ ከዚህ ጋር እኩል የፖለቲካ ተቋማት አቅም ካላደገ ውጤቱ አለመረጋጋት ይሆናል፤ ጠንካራ ተቋማት ከሌሉ ፖለቲካዊ ትግል ወደ ኃይል ርምጃ ይሸጋገራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመጽሐፋቸው ከልወደድ ባይነት ይልቅ ጠንካራ ተቋማት ሊገነቡ እንደሚገባ፣ እነዚህ ተቋማት ምክንያታዊነትና ተጠየቅን ሲያረጋግጡ ፖለቲካው ወደ ሰለጠነ መንገድ እንደሚጓዝ ያስረዳሉ።
ሀሳብ ዐልቦነት በአንዴ የሚከሰት ሳይሆን ሒደት ወለድ ነው፡፡ የተዛባ ትርክት ፅንፈኝነትን ይመግባል፤ ፅንፈኝነት የተበላሸ ፖለቲካዊ ባህልን ያባዛል፤ የተበላሸ ባህል የጥቅም ትስስርን ያጸናል፤ የጥቅም ትስስር ተቋማትን ያዳክማል፤ የተዳከሙ ተቋማት ደግሞ ለተበታተነ መረጃና ለሕዝበኝነት ለም መሬት ይሆናሉ።
በመጨረሻም ፖለቲካው ወደ አግላይ ሽኩቻና ወደ መሳሪያ ንግግር ይሸጋገራል። መዳረሻውም የተቋማት ድቀት፣ የተከፋፈለ ማህበረሰብ፣ ኢፍትሃዊነት መንገስ፣ ከብልፅግና ይልቅ ጉስቁልና ነው።
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት፤ ጀግንነት፣ ለም መሬትና በቁጥር የበዛ አምራች ሃይል አላት። ለዚህ ትልቅነት ያልመጠነ የድህነት ስም ያላበሳት ግን ደጋግሞ የተመለሰው ይኸው ሀሳብ ዐልቦነት ነው።
የታዩ የለውጥ ተስፋዎችም በጮርቃነታቸው እንዲቀጩ ያደረገው ይህው መንገድ ነው።
ከዚህ ወጥመድ ለመላቀቅ ብቸኛው መንገድ ጠንካራ፣ ገለልተኛ ተቋማትን በመገንባትና ሀሳብን በሀሳብ በሚሞግት ምክንያታዊ ፖለቲካዊ ባህል መተካት ነው።
የመደመር መንግሥት ይሄንን ፖለቲካዊ ባህል “የሃሳብ ልዕልና” ይለዋል።
በአፈወርቅ እያዩ

