አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልል ሕዝብ ሕገወጡ የህወሓት ቡድን በክልሉ እያደረሰ ያለውን ግፍና መከራ ለማስቆም እያደረገ ያለውን ትግል ማጠናከር አለበት አሉ የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ ሊቀ መንበር ከበደ አሰፋ።
ሕገወጡ ቡድን ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የጥፋት ጥምረት መመስረት ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር በማራቅ ለደህንነት ስጋት ከዳረገበት እኩይ ተግባሩ የቀጠለ ተልዕኮ የማስፈጸም ሂደት መሆኑን ተናግረዋል።
ሕገወጥ ቡድኑ “ፅምዶ” በሚል ስም ከሻዕቢያ የጥፋት ሀይል ጋር የፈጠረው የጥፋት ጥምረት ኢትዮጵያን ለማፍረስና ከዘላቂ ልማቷ ለማደናቀፍ የተወጠነ የባዕዳን ተልዕኮ መሆኑን አንስተዋል።
ይህ ያልተቀደሰ ጥምረት መመስረቱ ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማቷን እንዳታረጋግጥና አሁንም ሀገሪቷን ለማመስ የተዘረጋ የባዕዳን ፕሮጀክት አካል መሆኑንም አመልክተዋል።
ቡድኑ ከምስረታው ጀምሮ ለሀገርም ሆነ ለትግራይ ክልል ሕዝብ ጥቅም መከበር ከመቆም ይልቅ ለባዕዳን ኃይሎች ተልዕኮ መገዛቱን ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያዊነት ሥነልቦና የነበራቸውንና ድብቅ አጀንዳውን የተረዱ የትግራይ ተወላጆችን በማጥፋትና በማስወገድ የፈጸማቸው እኩይ ተግባራቱ ለዚህ ማሳያ መሆኑን አክለዋል።
የህወሓት የጥፋት ቡድን የፕሪቶሪያውን ስምምነት መጣሱና የጥፋት መንገድ መከተሉ የሕገወጥ ቡድኑን ለባዕዳን የመላላክ ተፈጥሯዊ ባህሪው መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
የውጭ ኃይሎችን ፍላጎት በትግራይ ክልል ወጣቶች መስዋዕትነት ለማስፈጸም የሚደረገው ጥረት በሕዝቡ እና በወጣቱ ንቃት ምክንያት እንደፈለገው ሊሳካ አለመቻሉን አንስተዋል፡፡
በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች በአንድነት በመቆም ቡድኑን በፍጥነት በማስወገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በውጭ ሀገር የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆችም አስፈላጊውን ተፅዕኖ በማሳደር ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ግፍና መከራ ለማስቆም መስራት እንዳለባቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

