አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ የሀገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጋራ የተቀረጸበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፡፡
አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን አስመልክተው ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አፈ ጉባኤው በእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸው፤ ይህ ጉባዔ ለነገዋ ጠንካራ ኢትዮጵያ መሠረት የተጣለበት እና የሀገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጋራ የተቀረጸበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የዚህ የምክክር ሂደት ዋና ዓላማ በሀገራችን ለረጅም ጊዜያት የግጭት መነሻ የሆኑ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በውይይት መፍታት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ምክክሩ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው አካታች እና አጠቃላይ ሀገራዊ መድረክ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
የምክክር ሂደቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወጣው አዋጅ ቁጥር 1265/2014 መሠረት ራሱን የቻለ እና ገለልተኛ የፌዴራል መንግሥት አካል ሆኖ በተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካይነት በሕጋዊ ሥርዓት መመራቱን አስታውሰዋል።
ኮሚሽኑ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ወረዳ እና ቀበሌ ድረስ በመውረድ አርብቶ አደሮችን፣ አርሶ አደሮችን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ማኅበራትን እና ዳያስፖራውን ያካተተ ሰፊ ሥራ ማከናወኑ የምክክሩን ተአማኒነት እና ሕዝባዊ ቅቡልነት ማረጋገጡን አብራርተዋል።
ከሕዝብ እና ከባለድርሻ አካላት በተሰበሰቡ አጀንዳዎች መሠረት ተለይተው በቀረቡ ስምንት ዐበይት ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከመላው ሀገራችን የተወጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሰፊ ምክክር በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።
በዚህም የኃይል እና የጦርነት ፖለቲካን በማስቀረት ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት እንደሚቻል ማሳየት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ጉባዔው በስኬት ሲጠናቀቅ ለሀገራችን ዘላቂ መፍትሔ የሚሆኑ በርካታ ዐበይት ምክረ ሐሳቦች መፍለቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ ምክረ ሐሳቦች ለቀጣይ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ ለሕገ መንግሥታዊ እና ተቋማዊ ለውጦች እንዲሁም ለዘላቂ እርቅ እና ብሔራዊ መግባባት መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የምክክሩ ዋነኛ ግብ የትናንት ታሪካዊ ስብራቶችን በማከም ለቀጣዩ ትውልድ ሰላሟ የተጠበቀ እና ብልጽግናዋ የተረጋገጠ ሀገር ማስረከብ በመሆኑ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና የመንግሥት አካላት ከምክክሩ የተገኙ ውጤቶችን በባለቤትነት በመጠበቅ ወደ ተግባር እንዲተረጉሟቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ለዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም በራሳቸው እና በምክር ቤቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

