አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለሀገር ግንባታ እና ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መሰረት ተጥሎበታል፡፡
በታላቅ ተስፋ ሲጠበቅ የነበረው እና ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አዲስ መሰረት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በዛሬው ዕለት ተጠናቅቋል፡፡
ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት በይፋ የተጀመረው ይህ የምክክር ሂደት ኢትዮጵያ የገጠሟትን ጥልቅና ውስብስብ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተከፈተ ታሪካዊ ዕድል ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ተመሳሳይ ሀገራዊ ምክክሮች ሙሉ በሙሉ በሁሉም ጉዳዮች ላይ መስማማት ላይ ተደርሶ ባይታወቅም በኢትዮጵያ የተካሄደው ምክክር ግን በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ላይ የተሻለ መግባባት ላይ የተደረሰበት ነው፡፡
ምክክሩ የማንኛውም ፓርቲ፣ የመንግሥት አካል ወይም የተለየ ቡድን የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ሳይሆን፤ ከሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከተቋማት፣ ከፌደራል፣ ክልልና ከተማ አስተዳደሮች፣ ከታዋቂ ግለሰቦች፣ ከቀድሞ ታጣቂዎችና ከዳያስፖራው ማህበረሰብ የተወጣጡ የተለያዩ ድምጾች በነጻነትና በእኩልነት የተስተናገዱበት መድረክ ነው፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ወገኖች ድምጽ አድምጦ ወደ ስኬት ያመራ የአንድ ወገን ድል ወይም የሌላው ሽንፈት ሳይሆን ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የሃሳብ ህብርን አቅፎ መቋጫውን ያገኘ ነዉ፡፡
መላው የኢትዮጵያ ህዝብም እስከዛሬ አላግባባ፣ አላቀራርብ፣ አልፈታ ያሉት ችግሮቹን በምክክር ፈትቶ የወደፊቷን የጸናች ኢትዮጵያ ለማየት የራሱን አስተዋፅኦ ያበረከተበት ይህ መድረክ ወደፊት ለፈጻሚ አካላት የሚቀርቡት ምክረ ሀሳቦች የድካሙን ዋጋ ይክሱታል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
የምክክር አዳራሽ ውስጥ ያልገቡ ዜጎችም ቢሆን በተወካዮቻቸው በኩል የላኳቸው እና መፈታት ያለባቸው ችግሮች ተፈተው
የምክክርን አስፈላጊነት በተግባር የሚረዱበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡
በእመቤት ሲሳይ

