Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በልጆቿ የምክክር ክር የተሸመነችው ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘመን ማህደር ውስጥ በታሪክ ብዕር በደመቀ ቀለም ከተጻፉ የዓለም ታሪክ ገጾች መካከል የኢትዮጵያ ስም ሁልጊዜም በግርማ ሞገስና በነጻነት ጎልቶ ይታያል።
ኢትዮጵያ የዉጭ ወረራ ያላስደነገጣት፣ የዘመናት ፈተና ያላንበረከካት፣ በልጆቿ የአንድነት ክር የተሸመነች የጥበብና የፅናት ተምሳሌት ናት።
ኢትዮጵያውያን በትናንት የታሪክ አደባባይ የጋራ ቤታቸውን ለማጽናት በጋራ ቆመዋል፤ ዛሬም በእልህ አስጨራሽ ፈተናዎች ውስጥ ሆነው ያንን የጋራ ቤት የመጠበቅ አደራቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፤ ነገም ለአፍታም ወደኋላ ሳይሉ ሉዓላዊነቷን አጽንተው ለትውልድ እንደሚያስረክቡ ጥርጥር የለውም።
የኢትዮጵያውያን የትናንት ድል መሠረቱ የአካል ጥንካሬ ወይም የጦር መሣሪያ ብልጫ ሳይሆን፣ በውስጣቸው የነበረው የማይበገር የነጻነት ጥማትና የኅብረት መንፈስ ነው።
በዓድዋ ተራሮች ላይም የምናኘው ትልቁ ምስጢር ልዩነትን አቅልጦ ሀገርን የማስቀደም ጥበብ ነው።
እንደሚታወቀው ማንኛውም በቤተሰብ ውስጥ አለመግባባቶችና ክርክሮች ሲፈጠሩ ጉዳዩን በሽምግልና ጥበብ የመፍታት የረጅም ጊዜ ባህል አለን።
ዛሬም ኢትዮጵያውያን በትልቁ የሀገራቸው ጉዳይ በጋራ መክረው፣ እንደ ትናንቱ ለሀገራቸው ክብርና ደኅንነት ሲሉ በጋራ አሸንፈዋል።
ሀገር ለማስቀጠል መፍትሔው የሚገኘው ከሌላ ቦታ ሳይሆን እርስ በርስ በመደማመጥና በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት መሆኑን በተግባር አሳይተዋል።
ኢትዮጵያ በሀገራዊ ምክክርና በውይይት አጥር ተከብባ፣ በውስጥና በውጭ ፈተናዎች ፈጽሞ የማትበገር፣ ይበልጥ የጸናችና ወደፊት በልማት የምትገሰግስ ሀገር ሆና ትቀጥላለች።
የኢትዮጵያ ትናንት የአንድነትና የድል ታሪክ፤ ዛሬዋ ደግሞ ፈተናዎችን በምክክር ያሸነፈች፤ ነገዋ ደግሞ የብልጽግና እና የጽናት ነጸብራቅ ሆኖ ይቀጥላል።
ለዘመናት በጦርነትና በአለመግባባት ስትፈተን የኖረችው ኢትዮጵያ በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግራና ተግባብታ ዛሬ በልጆቿ የምክክር ክር ተሸምና አሸብርቃለች።
ኢትዮጵያ አሸንፋለች!
በሶስና አለማየሁ
Exit mobile version