Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

“ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ኢትዮጵያ በተግባር አሳየች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አንዳንድ ደማቅ ድሎች በጦር ሜዳ አይመዘገቡም ፤ አንዳንድ ታሪኮች የሚጻፉት በጥይት ድምጽ ሳይሆን በምክክር ጠረጴዛ ዙሪያ በሚነሱ ድምጾች ነው፤ ኢትዮጵያም ይህንን እውነት ለራሷም ለዓለምም በተግባር አስመስክራለች።

“ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለው መርህ ከቃል በተሻገረ ኢትዮጵያ በተግባር የደመቀችበት ፍልስፍና ሆኗል።

የዘመናት ቁርሾዎቿን፣ የተጠራቀሙ ቁስሎቿንና የተወራረሱ ልዩነቶቿን በጠመንጃ ሳይሆን በምክክር ፈታች። ደም ሳይፈስ፣ ወገን በወገን ላይ ሳይነሳ፣ ከየማዕዘኑ የተውጣጡ አራት ሺህ ኢትዮጵያውያን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የሀገራቸውን ነገ በራሳቸው ቀረጹ።

ይህ ድል የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ ግጭት ተብትቧቸው፣ በድህነት አዙሪት ተተብትበው ለሚቆራቆዙ አፍሪካዊ እህት ወንድሞቻችን ብርሃን የፈነጠቀ ተምሳሌትነት ነው።

አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ ልጆች፣ በራሷ ጥበብ፣ በራሷ ዕውቀትና ፍልስፍና የመፍታት አቅም እንዳላት ያስመሰከረ ደማቅ ማሳያ ነው።

ችግሮቿ ከውጭ በሚመጣ መፍትሄ ሳይሆን፣ በራሷ ልጆች አቅምና ውሳኔ ሊፈቱ እንደሚችሉ ያረጋገጠም ታሪካዊ አብነት ነው።

በዚህ ታሪካዊ ሁነት የተነሳ ዛሬ ዓለም ኢትዮጵያን በተለየ ዓይን እንዲመለከታት ተገዷል፡፡ ለዘመናት ያንገሸገሹ ችግሮቿን በንግግርና በምክክር የፈታች ሀገር ተብላ ትታወሳለች።

“ንግግር ጊዜ ይወስዳል፣ ግን ግጭት የበለጠ ዋጋ ያስከፍላል”

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ይህንን ታሪካዊ ምክክር ለመላው አፍሪካ ትልቅ ተምሳሌት ሲሉ መስክረዋል።

ኢትዮጵያውያን ሰላምን ለማምጣት መነጋገርንና መመካከርን መምረጣቸው የሚደነቅ ተግባር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው፣ ምክክር የቱንም ያህል ጊዜ ቢፈጅ፣ ከግጭትና ጦርነት ጉዳት አንጻር ሲመዘን ዋጋው እጅግ የላቀ መሆኑን አስምረውበታል።

“ኢትዮጵያውያን እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትነው ያለፉ ናቸው”

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታም በበኩላቸው፣ ሂደቱን በቅርብ ሲከታተሉ እንደቆዩና በእጅጉ እንዳስደመማቸው መስክረዋል። አፍሪካ ታላላቅ ትልሞችን የማለምና የራሷን የወደፊት እጣ ፈንታ በራሷ የመወሰን አቅም እንዳላት ገልጸው፣ ይህ ስኬታማ ምክክር ለዚያ አቅም ህያው ማሳያ ስለመሆኑን “እኔም ምስክር ነኝ” በማለት ነው ያረጋገጡት።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አዲስ ምዕራፍ ስትከፍት ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም፤ ከዓድዋው አንጸባራቂ የነጻነት ድል እስከ ዛሬው ሃገራዊ የምክክር መድረክ ብሎም በራስ አቅም እስከተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ህያው ማስረጃዎች ናቸው፡፡

ዛሬም እንደገና፣ አህጉሪቱ ኢትዮጵያን በተስፋ ዓይን ትመለከታለች በጦር ሜዳ ሳይሆን በምክክር ጠረጴዛ የተገኘውን ድል እያየች፣ ከዚያም የራሷን ትምህርት እየቀሰመች።

የአፍሪካ መፍትሄ ከአፍሪካ ይመነጫል፤ ኢትዮጵያ ይህንን በተግባር አረጋግጣለች፤ ተራው የቀጣዮቹ ነው።

Exit mobile version