Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲስ የፖለቲካ ባህል – መመካር ቤት ያጠነክር

ለ40 ቀናት ያህል ከአራቱም ማዕዘናት የተሰባሰቡ ልጆቿ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ መክረውና ዘክረው አዲስ ታሪክ ጻፉ፡፡

ስለጋራ ቤታችን ስለ ኢትዮጵያ መጻኢ ጊዜ እና ስለ አንድነታችን ሲሉ ተወያዩ፣ ተደማመጡ፣ ሐሳብ አዋጡ፡፡ ይህ በሀገራችን ታሪክ ተደርጎ የማያውቅ እና አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍን የከፈተ ተግባር ሊባል ይችላል፡፡

ይህ ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠሟታትን የፖለቲካና ማህበራዊ ልዩነቶች በውይይትና በሕዝባዊ መግባባት ለመፍታት የጀመረችው ሀገራዊ የምክክር ሂደት፣ ለሀገሪቱ ሰላምና ዘላቂ ልማት ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ በኃይለ-ቃል ጀምሮ በኃይለ-እርምጃ የሚደመደምበትን አዙሪት ሰብረን በንግግርና በውይይት የምንተካበት ወቅት ላይ እንገኛለን” እንዳሉት ሂደቱ የሀገሪቱን የፖለቲካ ባህል ከኃይል አማራጭና ከግጭት አዙሪት ወደ ሰላማዊ ውይይትና መደማመጥ ለመቀየር ያለመ ጥልቅ ታሪካዊ ጥረት ነው፡፡

በምክክር ሂደቱ ለሀገርም ይሁን ለአፍሪካ አህጉር የሚጠቅሙ በርካታ አብነቶች ተወስደውበታል፡፡ የመጀመሪያው በልዩነቶች እና በጥያቄዎቻቸው ዙሪያ ህብረተሰቡ እርስ በእርስ የመደማመጥና የመከባበር ባህል መጎልበቱ ነው፡፡

ረጅም ዕድሜ ያላቸውን ጥልቅ ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት ከተደረጉ የታሪክ ስህተቶች ይልቅ ተቀራርቦ በመነጋገር የጋራ መፍትሔ መፈለግ ዘላቂ ሰላም እንደሚያመጣ ሂደቱ በተግባር አሳይቷል፡፡

ሌላኛው ከምክክር መድረኩ የተገኘው ልምድና ተሞክሮ የሂደቱ አሳታፊነትና ሕዝባዊ ባለቤትነት ነው፡፡ የምክክር ሂደቱ ከአራቱም ማዕዘናት የመጡ ተመካካሪዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና ልዩ ልዩ የፖለቲካ ኃይሎችን በስፋት ማሳተፍ በመቻሉ፣ ምክክሩ የጥቂት የፖለቲካ ምሁራንና አመራሮች ብቻ ሳይሆን የመላውን ሕዝብ ድምፅ የተሰማበት እንዲሆን አስችሏል፡፡

በመጨረሻም በመሠረታዊ የሀገረ መንግሥት ግንባታና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ በግልጽ የመወያየት ልምድ መዳበሩ ሲሆን ይህም ለኢትዮጵያ ሰላም፣ አንድነት እና ልማት አስተማማኝ መሠረት የሚጥል ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ይህን አንጸባራቂ ድል በአግባቡ በመጠበቅ የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ንቁ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡

ይህን ድል ሰላምን በማስከበር፣ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን በማስጠበቅ እና ድህነትን ድል ለማድረግ በምናደርገው እልህ አስጨራሽ ትግልም መደገም ይገባዋል፡፡

Exit mobile version