አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር ከስሜት፣ ከደም እና ከሥነ ልቦናዊ ቅኝት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ሕያው ማንነት ነው።
የሰው ልጅ ከሀገሩ ጋር ያለው ትስስር የእምነትና የሕልውና ያህል የጠነከረ ነው። ለዚህ ነው ለብዙዎቻችን ነገራችንና ጉዳያችን የምትሆነው፡፡
ኢትዮጵያ ታዲያ የሥነ ልቦናችን ስሪት የተገነባበት፣ የማንነታችን የተቀረጸበት፣ በዕውቀት የታነጽንበት፣ የተዳርን፣ የተኳልንባት ታላቅ የእናት እቅፍ ናት።
ሀገራችን ሲከፋን የምንተዋት፣ ሲደላን የምናጌጥባት ሳትሆን በጥብቅ ቃል ኪዳን የተሳሰርናት የማንነታችን ማህተም ናት፡፡ ለችግሯ ጊዜ ስትፈልገን አለሁልሽ አለማለት የእኛ መልካችንም ልካችንም አይደለም።
ትናንት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመጀመሪያውን ታሪካዊ የምክክር ምዕራፍ በስኬት ባጠቃለለበት ታላቅ መድረክ ላይ፣ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ያነሱት ሀሳብ የብዙዎችን ስሜት ኮርኩሯል፤ የሀገርንም ፍቅር ጥልቅነት ዳግም አበስሯል።
ኮሚሽነሩ በቤተሰብ ሐዘን ምክንያት ለጥቂት ቀናት ወደ ውጭ ሀገር ባቀኑበት ወቅት፣ «ምክክሩን ጥለው ጠፉ፤ ከሀገር ኮበለሉ» የሚሉ ሀሰተኛ ዘገባዎች ተሰራጭተውባቸው ነበር። መቼም ለሐሰተኛ መረጃ አሰራጮቹ “በሬ ወለደ” ብርቃቸው አይደልም። “ወደቀ” ሲባል “ተሰበረ” እንጀራቸው ነው።
መስፍን አርዓያ(ፕ/ር) ትናንት በልዩ ሕዝባዊ ኃላፊነት ወደ መድረኩ ተመለሱ፡፡ የተነዛውን ሀሰተኛ መረጃ በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት ሲገልጹ፣ «ከሀገሬ አልሸሸሁም፤ ከሀገሬ ምንጊዜም አልሸሽም፤ ከሀገሬ ምንጊዜም አልኮበልልም! እንኳን በዚህ ዕድሜ፣ የዛሬ አርባ ዓመት ጉልበት በነበረኝ ጊዜ፣ መውጣት በምችልበት ወቅትና እህት ወንድሞቼ ውጭ ባሉበት ጊዜም ቢሆን ከሀገሬ አልወጣሁም። የቀረችኝን ዕድሜ እዚሁ ነው የማሳልፈው!» ብለዋል፡፡
ይህ ተራ ንግግር አይደለም። ይልቁንም ዕድሜያቸውን ሙሉ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ያገለገሉ፣ ከታመመው ጋር የታመሙ፣ አያሌዎችን ተስፋ ያለመለሙ፣ ከመከረው ጋር የመከሩ ልብ የሚነካ የሀገር ፍቅር የተግባር ቃል እንጂ።
እዚህ ጋር አንድ ጥያቄ እንጠይቅ፣ በእርግጥስ ከኢትዮጵያ ወዴት ይጠፋል? እንደ መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ያሉ አባቶች የሚያስተምሩን ትልቅ እውነት ቢኖር፡ ሀገር ችግር ሲገጥማት ጥሎ አይሸሽም፤ ይልቁንም ፈውስ ለመሆን በጽናት ይቆማል። ፕሮፌሰሩና ባልደረቦቻቸው ኢትዮጵያ እንድትፀና አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍተዋል፤
ይህንን ጥብቅ ሀገራዊ ትስስርና የፍቅር ዕዳ የከበደውን የቆራጥነት ስሜት ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ «ሀገሬ» በሚለው ዘመን ተሻጋሪ ግጥሙ ተቀኝቶበታል፣
«ብሞት እሄዳለሁ እመሬት ብገባ፣
እዚያ ነው አፈሩ የእማማ የአባባ፤
ስሳብ እሄዳለሁ ቢሰበርም እግሬ፣
አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ ሀገሬ።»
ከትውልድ ሀገር ጋር ያለ ቀጠሮ በምንም ዓይነት ወሬና ውሸት የሚበጠስ አይደለም። ሐሰተኛ መረጃዎችና የሰዎች አሉባልታ በየቀኑ ቢነፍሱም፣ ለሀገር የሚደረግ እውነተኛ አገልግሎት ግን በቆራጥነትና በተግባር የሚታይ ነው።
ዋና ኮሚሽነሩ በሐዘን ላይ ሆነውም ቢሆን ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የምክክር ኮሚሽኑን ታሪካዊ ፍጻሜ በውጤታማነት እንዲደመደም ማድረጋቸው፣ ለወሬኞች የተሰጠ ከባድና ተግባራዊ ምላሽ ነው።
ይህ የቁርጠኞችና የባለአደራዎች መንገድ ነው። የትኛውም ትውልድ ቢሆን ከዚች ሀገር ሕመም ጋር ተጋምዶ መፍትሔ ከመፈለግ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም።
የመስፍን አርዓያ(ፕ/ር) አባባል የሚያስገነዝበን፣ የቀረችውንም ዕድሜ ቢሆን ለሀገር መኖሪያ ማድረግ ትልቅ የታሪክ ባለአደራነትና የስብዕና መሰረት ነው። በእርግጥም ከኢትዮጵያ ወዴት ይሸሻል?
በአፈወርቅ እያዩ

