የሀገር ሕመም የገዘፈው፣ ስብራቱም የሰፋው ታሪካዊ ጠላቶች በከፈቱት አሉባልታና ሴራ ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም የገዛ ልጆቿ የሀሳብ መድረክ አጥተው፣ እርስ በርስ መደማመጥ ተስኗቸው በየጎጇቸው በገነቡት የእኔነት አጥር ጭምር እንጂ።
የሕብራዊነት ማሕደር፣ የባሕልና የታሪክ እልፍኝ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ ግን የዘመናት የፖለቲካ ስብራቷን የምትጠግንበት አዲስና ስልጡን ጥበብ አግኝታለች ፤ ይህም የመደማመጥ ጥበብ ነው።
ሀገርን የማፅናት ታላቅ ተልዕኮ የጋራ መግባባትን ሲጠይቅ፣ ዜጎች ከጠበበው የስሜት ቅጥር ወጥተው በጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ ተመክክረው አሸንፈዋል። ኢትዮጵያውያን በጉልበት ሳይሆን በሀሳብ የበላይነት፣ በጠብመንጃ ሳይሆን በውይይት ሀገራቸውን በፅኑ መሰረት ላይ ገንብተዋል።
ይህ የጠረጴዛ ዙሪያ ትዕይንት እና የምክክሩ ውጤት በተግባር ሲታይ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ አሸናፊነት በጉልህ ያረጋገጠ ነው። ለዘመናት በጠብመንጃ አፈሙዝና በድብቅ ሴራ ይፈቱ የነበሩ የፖለቲካ ጥያቄዎች፣ በሰላማዊ የሀሳብ ፍልሚያ መድረክ ላይ ቀርበው ስምምነት ላይ ተደርሶባቸዋል።
በምክክሩ አማካኝነት ልዩነቶች ሀገር ማፍረሻ ሳይሆኑ ሀገር ማድመቂያ መሆናቸውን ሕዝቡ በተግባር አሳይቷል። የተሰበሩ ድልድዮች ታድሰዋል፣ ቁስሎችም በይቅርታና በማስተዋል ተጠግነዋል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የመፍታት አቅም እንዳላቸው በማሳየት፣ የውጭ ኃይላት “የአደራዳሪነት” ጭምብል አውልቀው የሀገር ሉዓላዊነትን እንዲያከብሩ አስገድደዋቸዋል።
ይህ ታላቅ የምክክር ውጤት የውስጥ ሰላምን ከማረጋገጡም በላይ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት በእጅጉ የሚያጎላ ነው ።
ታዲያ በኢትዮጵያውያን ተመካክሮ ማሸነፍ እና በውይይት ሀገር ማፅናት ምክንያት ክፉኛ የከሰሩት እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶቻችን አሁን ምን ይላሉ? በመጀመሪያ ደረጃ የክህደት ስሌታቸው እንደፈረሰ ይውጡታል።
ኢትዮጵያን በልዩነቶቿ ማጥፋት ይቻላል ብለው በቢሊየን የሚቆጠር በጀት የመደቡ የውጭ ኃይላት፣ ዛሬ ያ የልዩነት ግንብ የውይይት ድልድይ ሆኖ ሲቀየር ፣ ባንዳዎችን በመግዛትና በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሀገር ለማፍረስ የሄዱበት ርቀት ሁሉ የኢትዮጵያን ጥልቅ ህዝባዊ መሰረት ማናወጥ እንዳልቻለ ሲረዱ፣ የታሪካችንና የትዕግስታችን ጥልቀት ግራ ያጋባቸዋል።
የጥፋት ሴራቸው ሳይሰራ ቀርቶ የምክክር እና የሰላም ድምፅ ሲበልጥ ታዝበዋል።እነሱ የሽንፈት መርዷቸውን በዝምታ ይቀበሉታል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርስ ሲደማመጥና የዘመናት ቁስሉን በራሱ ልጆች እጅ ሲጠግን፣ እነሱ ሰላሙን የሚነጥቁበት ምክንያት ያጣሉ። ጀትም ሆነ በጀት የማይበግረው የውስጥ አንድነት ሲፈጠር፣ በኢትዮጵያ ድል የከሰሩት ጠላቶች በፀጥታና በታሪክ ህሊና ተሸንፈው ከመመልከት ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖራቸውም።
የኢትዮጵያ አዲሱ ምዕራፍ እነሱን ተስፋ የሚያስቆርጥ፣ ለባንዳዎቻቸውም የሞራል ስብራት የሚሆን ነው። አዎ፣ ኢትዮጵያውያን ተመክክረው አሸንፈዋል፤ በውይይትም ሀገር አፅንተዋል! ሰማዩ የጠራ ነው፤ አሞራዎች የሚቀናጁበት የጥፋት ጭስ ከእንግዲህ አይታይም!
በኃይለኢየሱስ መኮንን

