አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት በሕዝባዊነት፤ በሥነ ምግባርና ሀገርን ባለማስደፈር ወኔውና ብቃቱ ደማቅ ታሪክ የጻፈ የሕዝብ ተቋም ነው፡፡
ይህ ሰራዊት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የሀገርን ዳር ድንበር በጽናት ከመጠበቅ ባሻገር በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተልዕኮዎች ላይ ባሳየው ብቃትና የላቀ የሥነ ምግባር ከፍታ ተመስክሮለታል፡፡
በመደመር መንግሥት ሰራዊቱን ዘመናዊ፣ ፕሮፌሽናልና ዘመኑን የሚመጥን የቴክኖሎጂ ባለቤት ለማድረግ የተካሄደው አጠቃላይ የመዋቅር፣ የሰው ሃይል እና የትጥቅ ሪፎርም አካል ከሆኑት ክፍሎች ውስጥ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ዋነኛው ነው፡፡
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ድንበር እና የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በተዘጋጁ ከፍተኛ የውጊያ እና የቴክኒክ ብቃት ባለው የሰው ሃይል የተዋቀረ የሀገር መከላከያ ቁልፍ አካል ነው።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህንን ዕዝ በአካል ብቃቱ፣ በጽናቱና በከፍተኛ ወታደራዊ እውቀቱ የውጊያ አቅጣጫ ቀያሪ ሲሉ ይገልጹታል፡፡
ይህ ዕዝ የኮማንዶ፤ አየር ወለድ እና ጸረ- ሽብር ክፍሎችን በማካተት የሀገርን ሁለንተናዊ ደህንነት ለማስጠበቅ ቀን ከሌት በጀግንነት ቆሟል፡፡
የዕዙ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ 45ኛ ዙር ሰልጣኞችን ባሰመረቁበት ወቅት ፤ ዕዙ የሚሰጠውን ግዳጅ በአስተማማኝ ብቃት በመወጣት የሕዝብ ልጅ መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል ብለዋል፡፡
በጠንካራ ሥነ ምግባር ዘመኑን የዋጀ ሥልጠና የወሰደ የኢትዮጵያ ደጀን እንደሆነም አውስተዋል፡፡
ይህ ዕዝ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወደ የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በፍጥነት በመንቀሳቀስ አስቸጋሪ እና ውስብስብ ተልዕኮዎችን የመፈጸም ብቃት አለው።
በሀገር ውስጥም ሆነ በድንበር አካባቢ የሚነሱ የሽብርተኝነት ስጋቶችን ማክሸፍ እና ድገተኛ የደህንነት አደጋዎችን መከላከል፤ በከባድ የመሬት አቀማመጥ ሳይበገር ቁልፍ የሆኑ የጠላት ዒላማዎችን ማጥቃት የሚያስችል ክህሎትን የታጠቀ ነው፡፡
በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወይም ስልታዊ ቦታዎችን ነጻ የማድረግ እና የማዳን ስራ ማከናወን፤ በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ታግዞ ምስጢራዊና ፈጣን እርምጃዎችን የመውሰድ አቅምን የተጎናጸፈ የሰራዊቱ ክፍል ነው።
የዚህ ዕዝ አባላት ከአካላዊ ጥንካሬ በላይ የአእምሮ ዝግጁነት እና የውሳኔ አሰጣጥ ፍጥነት ያላቸው ናቸው።
በጽኑ ስነ-ምግባር፣ በጠንካራ የውጊያ ጥበብ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቁት የዕዙ አባላት፣ በየትኛውም አስቸጋሪ የአየር ጠባይ እና የመሬት አቀማመጥ ውስጥ ውጤታማ ተልዕኮን የመፈጸም ችሎታን ተጎናጽፈዋል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በተከወነው ሪፎርም የመጣውን ውጤት እና የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት የዘመናዊነት ጉዞ ብሎም ዝግጁነት የሚያሳይ መስታወት ነው፡፡
በመልካም ፈቃዱ

