Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያና ጀርመን የኢነርጂ አጋርነት የፈጠራ ውድድር ፕሮግራም ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 27 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ጀርመን የኢነርጂ አጋርነት ፕሮግራም በኢነርጂ ዘርፍ የፈጠራ ውድድር ይፋ መሆኑን የዉኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የፈጠራ ውድድሩ ይፋ የሆነው ከ90 በላይ የኢትዮጵያና የጀርመን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ተወካዮች፣ የግል ዘርፍ ተሳታፊዎች እና በፈጠራ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች በተሳተፉበት በበይነ መረብ በተካሄደበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል።

“ያልተማከለ የኢነርጂ መፍትሔ” በሚል መሪ ቃል በበይነ መረብ በተካሄደው በዚህ ፕሮግራም÷ የፈጠራ ውድድሩ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች ይፋ መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው ።

ውድድሩ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን ተደራሽነት ለማስፋትና ለገጠሩ ነዋሪዎች ጭምር ለማድረስ የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ተብሏል።

ከዚያም ባለፈ የሚቀርበው የፈጠራ ሥራ ከአካባቢ ብክለት የጸዳ፣ አስተማማኝ ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ እንዲሁም አስፈላጊ ለሆኑ ዘርፎች መሆኑን አመላክቷል።

ይህም ለጤና፣ ለውኃ፣ የኮቪድ ሥርጭትን ለመከላከል የሚያግዝና በዘላቂነት ሊያገለግል የሚችል ዓይነት መሆን እንዳለበትም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያና ጀርመን የኢነርጂ አጋርነትና ትብብር በአውሮፓውያኑ ከህዳር 2019 በኢትዮጵያ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና በጀርመን የኢኮኖሚ ጉዳዮችና ኢነርጂ ሚኒስትር ፒተር አማካኝነት ተፈርሞ የተጀመረ የትብብር ሥምምነት መሆኑም ነው የተገለጸው ።

ውድድሩን በሚመለከት ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ከ‹‹ Ethiopian-German Energy Partnership›› ድረ -ገፅ ማግኘት እንደሚቻል ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version