Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የምክክሩ ታሪካዊነት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ውስብስብና ዘመናት የተሻገሩ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስብራቶች በአንድ ጀንበር የተፈጠሩ አይደሉም፤ በመሆኑም በአንድ ጀንበር አያበቁም።
የቆዩ ታሪካዊ ቁስሎችን ማከም፣ የተከማቹ ቅሬታዎችን መካስና የላላውን ማህበራዊ መዋቅር መልሶ መገንባት ከፍተኛ ጊዜን፣ ትዕግስትንና ሀገራዊ ርብርብን የሚጠይቅ ረጅም ጉዞ ነው።
በቅርቡ ውይይቱን በስኬት መቋጨቱን ይፋ ያደረገው ሀገራዊ የምክክር ሂደት፣ በታሪካችን ውስጥ ትልቅ የዕድገት ነጥብ ሆኖ ይመዘገባል።
ይህ መድረክ ከጥንት ጀምሮ ችግሮችን በመነጋገር ከመፍታት ይልቅ ጠብመንጃ መወልወል ለለመደው የፖለቲካ ባህላችን “መፍትሔያችን ንግግርና ውይይት ብቻ ነው!” የሚል ቁርጠኛና ታሪካዊ መልዕክት ያስተላለፈ ድል ነው።
ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነው ሀገራዊ የምክክር መድረክ፣ በተለያዩ ወቅቶች ብቅ ብለው በጥርጣሬና ባለመተማመን ዳመና ከከሰሙት የሰላም ጭላንጭሎች የሚለየው፤ አለመነጋገርን በጽኑ መሠረት ላይ ሆኖ በመካድ፣ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይትን ይፋዊ መደምደሚያ ማድረጉ ነው።
“መጀመር ነው ከባዱ” እንደሚባለው፣ ይህንን ሰላማዊ መንገድ በቅብብሎሽ ማስቀጠልና ማጠናከር የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።
ከ4 ሺህ በላይ ዜጎች በቀጥታ በተሳተፉበት በዚህ ታሪካዊ ሒደት፣ የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ መሠረታዊ አጀንዳዎች ተነስተው ሰፊ ምክረ ሐሳቦች ተሰንደዋል።
ሒደቱም ለዘመናት የዘለቁ ስር የሰደዱ አለመግባባቶችን በኃይል ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ትልቅ በር ከፍቷል።
ይህ ስኬት ግን የኢትዮጵያ ውስብስብ ችግሮች ሁሉ በአንዴ ተፈትተዋል ማለት አይደለም። ይልቁንም ለዘላቂ ሰላም፣ ለሰላማዊ የችግር አፈታትና ለዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ የማዕዘን ድንጋይ ተጥሏል ማለት ነው።
የቆዩ ሽኩቻዎች በአንዴ ባይጠፉም፣ የሐሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት ማስተናገድ እንደሚቻል አዲስ የተስፋ ብርሃን ፈንጥቋል።
ቀሪ ችግሮችም በቀጣይ በሚደረጉ አካታች ንግግሮች እየተፈቱ እንደሚሄዱ ትልቅ እምነት ይጥላል።
የዚህ ሒደት መሳካት ኢትዮጵያውያን ተቀምጠው በጋራ ሀገራቸው ላይ መምከር እንደሚችሉና ከኃይል አዙሪት ወጥተው በሰለጠነ መንገድ መተማመን እንደሚችሉ ያሳየ ትልቅ የምስራች ነው።
በአፈወርቅ እያዩ
Exit mobile version