Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ቱሪዝም በመደመር መንግሥት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ተፈጥሮ በወርቅ ብዕሯ ያሸበረቀቻት፣ ታሪክ በክብርና በግርማ ያነጻት፣ የአስራ ሶስት ወር ጸጋ ባለቤት፤ የሰው ዘር መገኛና የጥንታዊ ጥበባት ማህደር ናት።
የዚች ታላቅ ሀገር የቱሪዝም ሀብት በቃላት ድርደራ የሚገለጽ ተራ ገጽታ ሳይሆን፤ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እሳታማ ምድር እስከ ምዕራብ አረንጓዴ ገበታ ድረስ እያንዳንዱን ተጓዥ በድንቅ አግራሞት የሚይዝ፣ የሚጨበጥና የሚዳሰስ እምቅ ኃይል ነው።
የአክሱም ድንቅ ሐውልቶች የቀደሙ አባቶቻችንን ምህንድስና እና የግዛት ግርማ ይመስክራሉ።
ከአንድ ወጥ ዓለት የተፈለፈሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትም፣ ጥበብና እምነት ውህደት ፈጥረው ጽንፍ የረገጡበት ተአምራት ናቸው።
በምስራቅ፣ ተፈጥሮ ከሰው ልጅ ጥበብ ጋር የተቀላቀለችበት የሶፍ ዑመር ዋሻ የጥበብን ጥግ ያሳያል።
ወደ አፋር ስንሻገር ደግሞ የዳሎል ቀለማትና የኤርታሌ የመሬት ውስጥ እሳት ድምቀት ሰውን ከምድር አውጥተው ሌላ የጠፈር አካል ላይ የረገጡ ያህል መንፈስን የሚያስደምም ተዐምራዊ ስሜት ይፈጥራሉ።
በተጨማሪም ሀገራችን በዓለም ላይ በሌላ ቦታ የማይገኙ ሃገር በቀል የእጽዋት፣ የአዕዋፍና የእንስሳት ዝርያዎች ማዕከላዊ መኖሪያ በመሆን የተፈጥሮ ተመራማሪዎችንና ቱሪስቶችን ቀልብ ትስባለች።
ይህንን ዘመን ተሻጋሪ የታሪክና የተፈጥሮ ሀብት ከወትሮው የዝምታና የመዘናጋት ካባ በማውጣት የመደመር መንግሥት ላለፉት ጥቂት ዓመታት የወሰደው የቆራጥነት ርምጃ የዘርፉን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል፤ ቱሪዝምንም የሀገራዊ ብልጽግና ዋና አምድ አድርጎታል።
ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ እነዚህ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ተፈጥሮ የሰጠችንን በረከት ወደ ዘመናዊ፣ ማራኪና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ወደጠበቁ የመዳረሻ ስፍራዎች ቀይረዋቸዋል።
የእንጦጦ ፓርክ፣ የወንጪ፣ የኮይሻ፣ የሃላላ ኬላ እና የጎርጎራ ፕሮጀክቶችም ተፈጥሮን ከማደነቅ ባሻገር ተፈጥሮን በመንከባከብና ለትውልድ በሚመች ውበት አዘጋጅቶ ማቅረብ እንደሚቻል ማረጋገጫ ሆነዋል።
የላሊበላ እና የጎንደር ፋሲለደስ ጥገና፣ የአባ ጅፋር ቤተ መንግስት እድሳት፣ እንዲሁም የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ዘመናዊ ቅርስ ጥበቃ፣ ታሪክን ከዘመናዊ የእንግዳ ተቀባይነት አገልግሎት ጋር አስተሳስረዋል።
ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ለማዘመንና መረጃዎችን ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ አገልግሎቶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በዲጂታል አማራጮች የታገዙ እንዲሆኑም ተደርጓል።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ የነበራትን እምቅ ሀብት ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ ጥንካሬና ፍጹም ሀገራዊ ምስል በመቀየር ላይ ትገኛለች።
የቀደመ ታሪካችን ግርማ ከዘመናዊ የልማት ርዕይ ጋር ተዋህዶ ሀገራችንን በዓለም ቱሪዝም መድረክ ላይ በደማቅ ብርሃን እያበራት ይገኛል።
በሶስና አለማየሁ
Exit mobile version