አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ1501ኛው የነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) የመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
በሀገራችንና በመላው ዓለም ለምትገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1ሺህ 501ኛው የነቢዩ መሐመድ ልደት (መውሊድ) በዓል አደረሳችሁ! አደረሰን!
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነብዩ መሐመድ የልደት በዓልን በማስመልከት ለሕዝበ ሙስሊሙ እንኳን አደረሣችሁ ሲል የመልካም ምኞት መልዕክት ያስተላልፋል።
ነብዩ መሐመድ ህይወታቸውን በሙሉ ለሰው ልጆች ምሳሌ ሆነው ያለፉ ነብይ እንደመሆናቸው መጠን ሕዝበ ሙስሊሙ ከነብዩ መሐመድ ህይወት በመማርና የእሳቸውን የእምነት አስተምህሮ በመከተልና ተምሳሌት በማድረግ ለሰው ልጆች ፍቅርና ሠላም እንዲኖር ሊተጉ ይገባል፡፡
ታላቁ ነብዩ መሀመድ በነበራቸው የላቀ ስብዕና እና በአስተምህሯቸው ይመክሯቸው ከነበሩት ዕሴቶች፤ በሰዎች መካከል ፍጹም ፍቅር፣ መቻቻል፣ ሠላም፣ ደግነት፣ መተሳሰብና መረዳዳት እንዲኖር ነው፤ እሳቸውም በፍጹም ፍቅር ሰዎችን ያለመከፋፈል የሚወዱ ነበሩ፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙ ይህን ታላቅ ስፍራ የሚሰጠውን የመውሊድ በዓል ሲያከብር ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመግባባትና በሠላም አብሮ የመኖር እሴቶችን መሠረት በማድረግ ሊሆን ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ሁለንተናዊ ዕድገትና የብልጽግና ጉዞ ለማስቀጠል የዜጎች አንድነት፣ መከባበርና በጋራ መቆም ወሳኝ ሚና አላቸው።
በመሆኑም ይህ ታላቅ 1ሺህ 501ኛው የመውሊድ በዓል የሚከበርበት ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪካዊና ሁለንተናዊውን ሀገራዊ ምክክር በተሳካ ሁኔታ በአካሄደችበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በመሆኑ ለበዓሉ ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል። ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያስተማሩት የሰላም፣ የዕርቅ፣ የውይይት እና የጋራ መግባባት እሴቶች ለሀገራዊ ውይይቶቻችንና መግባባቶቻችን ጠቃሚ ግብዓቶች ናቸው።
በመሆኑም በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳትና በመተሳሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና አንድነት በጋራ ለመቆም ቃል በመግባት መሆን ይኖርበታል።
በመሆኑም ምክር ቤቱ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች መልካም የደስታና የሰላም በዓል እንዲሆንላቸው እየተመኘ፣ ይህ በዓል የሀገራችንን ሰላም ይበልጥ የምናጠናክርበት፣ ለአብሮነትና ለልማት በጋራ የምንቆምበት እንዲሆን ጥሪውን ያስተላልፋል።
በድጋሚ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ መልካም የመውሊድ በዓል እንዲሆን ምክር ቤቱ ከልብ ይመኛል!
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

