አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰሞነኛው ከካይሮ የሚሰሙት ተደጋጋሚ እና መሠረተ ቢስ ውንጀላዎች የኖረውንና ያረጀውን የፖለቲካ ትርክት እንደገና ለማደስ የሚደረጉ የከንቱ ጥረቶች ማሳያ ናቸው።
ግብፅ አሁንም ድረስ የታላቁን የዓባይ ወንዝ ተፈጥሯዊና ሕጋዊ ፍሰት እንደ ግል ሐይቋ አድርጋ ለመመልከት የምትሞክርበት መነፅር፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይሠራ፣ በቅኝ ግዛት ዘመን የተሠራ አሮጌ መነፅር ነው።
ይህ አመለካከት በፍትሐዊነት ላይ የተመሠረተውን ቀጣናዊ እውነታ የሚክድ ከመሆኑም በላይ፣ የወንዙ እውነተኛ ባለቤቶች የሆኑትን በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ሕይወትና መሥዋዕትነት ያጣጣለ ነው።
ዓባይ ለኢትዮጵያውያን ተራ የወንዝ ፍሰት ወይም የውሃ ስብስብ ብቻ አይደለም። ዓባይ የኢትዮጵያውያን የዘመናት የደም፣ የእንባ እና የላብ ጠብታ ድምር ውጤት ነው።
ላለፉት አሥርት ዓመታት፣ በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ዜጋ ካለው ጥቂት ገቢ ላይ ቀንሶ፣ ጉሮሮውን ዘግቶና ፍላጎቱን መሥዋዕት አድርጎ ነው ይህንን ታላቅ ታሪክ የገነባው።
እናቶች በወሊድ ምክንያት በጨለማ እንዳይቀሩ፣ ሕፃናት በኩራዝ ብርሃን ከማንበብ ተላቀው ወደ ዘመናዊው ዓለም እንዲሸጋገሩ እና ሀገሪቱ ከድህነት ቀንበር እንድትላቀቅ የተከፈለ የላብና የእንባ ዋጋ ነው።
ኢትዮጵያ የሌሎችን የመኖር መብት ሳትጋፋ፣ የራሷን ሕዝብ ከጨለማ የማውጣትና የልማት ሉዓላዊ መብቷን ስትጠቀም በካይሮ በኩል የሚሰነዘሩት ክሶች የሕዝቧን የጋራ መሥዋዕትነት የሚክዱ ናቸው።
የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ኢትዮጵያን ያላካተቱና ዛሬ ላይ ተፈጻሚነት የሌላቸው መሆናቸውን በመገንዘብ፣ ካይሮ የሀገሪቱን የልማት ጉዞ በሐሰተኛ ትርክቶች ለማደናቀፍ የምታደርገው ጥረት ፍሬ አልባ ነው።
የኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ፅናት እና በገንዘባቸውም ሆነ በጉልበታቸው ያፈሰሱት የላብ ጠብታ ዛሬ ዓባይን ወደ ብርሃን ምንጭነት ቀይሮታል።
ስለሆነም ከሰሞኑ የሚሰሙት የካይሮ መሰረት ቢስ ውንጀላዎች የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማትና ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም መርሕ ሊያስቆሙ አይችሉም። ዓባይ በጋራ የመልማትና የመለወጥ ተምሳሌት እንጂ በአሮጌ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የአንድ ወገን የበላይነት መፈተኛ ሊሆን አይገባም።
የኢትዮጵያውያን የደም፣ የእንባና የላብ ዋጋ የሆነው ይህ ታላቅ ወንዝ፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የሕዝቦቿን የብልጽግና ተስፋ እያበሰረ መፍሰሱን ይቀጥላል።
በኃይለኢየሱስ መኮንን

