Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ብስራት እየመጣ ነው?

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የብስራት ዘመን በተጨባጭ የልማት ቋጥኞች ላይ እየታነጸ ያለ የዘመናችን ህያው እውነት ሆኗል ።

ሀገራችን የትናንት የፖለቲካ ስብራቶቿን በሀገራዊ ምክክር ጠግና፤ በብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ መዋቅር ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች ነው፤ የጀመረቻቸውን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችም ከዳር እያደረሰች ትገኛለች።

ይህ ሁለንተናዊ ሽግግር ከመስከረም ወር የአዲስ ዓመት መባቻና ከአዳዲስ ብሔራዊ ተስፋዎች ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያን የትንሣኤ ብስራት በጉልህ እየስተጋባ ነው።

የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መነቃቃት በወረቀት ላይ በሰፈረ ምኞት ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ይልቁንም በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) እና በዓለም ባንክ ጭምር እውቅና የተሰጠው ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ግንባር ቀደም ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች፤ በዚህም የዓለም መሪዎች የሀገሪቱን መፃኢ የብልጽግና ጉዞ በትኩረት እየታዘቡት ይገኛሉ።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ኢትዮጵያን “የአፍሪካ ዕድገት ስትራቴጂያዊ መልሕቅ እና የአውሮፓ-አፍሪካ ትስስር ዋነኛ ምሰሶ” ሲሉ ገልጸዋታል፡፡

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ደግሞ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ስትራቴጂያዊ አጋርነት በማሸጋገር ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላትን ግንባር ቀደም ሚና አጉልተዋል።

በተመሳሳይ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት አማኑኤል ማክሮን የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያና የስትራቴጂያዊ ፕሮጀክቶች ትግበራ የወደፊቷን አፍሪካ የዕድገት አቅጣጫ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን መስክረዋል።

ይህ የሀገሪቱ የነገ ብሩህ ተስፋ በተጨባጭ መሬት ላይ በሚታዩ ዘርፈ ብዙ ስራዎችና ግዙፍ ፕሮጀክቶች ዕለት ከዕለት እየተገነባ ይገኛል።

ከእነዚህም ማሳያዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፤ ሀገሪቱን ከተረጂነት አዘቅት አውጥቶ የኃይል ማመንጫና የቀጣናው የኢኮኖሚ ሞተር የመሆን መፃኢ ዕድሏን በሚገባ አረጋግጧል።

በተጨማሪም በቢሊየን ዶላሮች በሚቆጠር ግዙፍ በጀት በቢሾፍቱ የሚገነባውና በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዓመት ከ110 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን በማስተናገድ ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ አቪዬሽንና የሎጂስቲክስ እምብርት ያደርጋታል።

በተጨማሪም ለሰው ሠራሽ አስተውሎት በተሰጠው ልዩ ትኩረት የኢትዮጵያ አዲስ ትውልድ ለነገው የዲጂታል ኢኮኖሚ ውድድር ራሱን እያዘጋጀ ይገኛል፡፡

የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶች ድብቅ የተፈጥሮ ጸጋዎቻችንን ወደ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መስህብነት ቀይረዋቸዋል።

በወርቅና በሌሎች ማዕድናት የተጀመሩት መዋዕለ ንዋዮች የውጭ ምንዛሪ አቅምን ሲያሳድጉ፤ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታና የኑክሌር ኃይል የማልማት ራዕይ የሀገሪቱን የሳይንስ ከፍታና የረጅም ጊዜ የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ ትልልቅ ምሰሶዎች ናቸው።

ይህ ኢኮኖሚያዊ ስኬትና ሀገራዊ ከፍታ ሙሉ ሊሆን የሚችለው የውስጥ አንድነትን በሚፈውሱና ስትራቴጂያዊ ራዕይን ባነገቡ የሰላም ርምጃዎች ጭምር ነው።

ሀገሪቱ ያለፉትን የፖለቲካ ቁርሾዎች፣ ልዩነቶችና ስብራቶች በሀገራዊ የምክክር መድረክ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት ወደ ዘላቂ መግባባት ለመድረስ ቆርጣ ተነስታለች።

ይህ አዲሱ የፖለቲካ ባህል፣ የተዘበራረቀውን የሀሳብ ገበያ አጥርቶ የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ ያስችላል።

ኢትዮጵያ በፈጣን ዕድገት ላይ ያለውን የሕዝቧን ግዙፍ ቁጥርና የኢኮኖሚ ፍላጎት የሚመጥን የባሕር በር ባለቤትነት ለማረጋገጥ ከአጎራባች ሀገራት ጋር በጋራ የመልማትና ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የዲፕሎማሲ ጥረት እያደረገች ነው።

ይህም የንግድና የጂኦፖለቲካ የበላይነትን የሚወስን፤ ለቀጣዩ ትውልድ በኩራት የሚሻገር ታሪካዊ ርምጃ ነው።

በጉባ ብስራት ይፋ ማድረጊያ ሥነሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያደረጉት ንግግር የዚህን አዲስ ዘመን ታላቅ መንፈስ በሚገባ ይገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው “ይህ የጉባ ብስራት የኢትዮጵያ ታሪክ የማይቀለበስ መሆኑን ያረጋገጠበት ታላቅ ምዕራፍ ነው፤ እኛ ወንዛችንን ስንገድብ ሌሎችን ለመጉዳት ሳይሆን የጨለማውን ዘመናችንን በብርሃን ለመተካት ነው” ነበር ያሉት፡፡

“ይህ ግድብ የኢትዮጵያውያን የደምና የላብ ውጤት ብቻ ሳይሆን፤ በአንድነት ከቆምን የማይቻል የሚመስለውን ተራራ መናድ እንደምንችል ማሳያ ነው፤ አዲሱ ዘመን የልፋታችንን ፍሬ የምንለቅምበት፣ የኢትዮጵያ ብስራት በዓለም አደባባይ ጎልቶ የሚሰማበት ይሆናል” ማለታቸው በሁሉም ኢትዮጵያውያን የልብ ትርታ የሚስተጋባ እውነት ነው።

ከመስከረም አዲስ ዘመን፣ ከአደይ አበባው ፍካት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ አሮጌውን የጥርጣሬ ምዕራፍ ዘግታለች፤ አዎ፣ የኢትዮጵያ ብስራት በእርግጥም እየመጣ ነው፤ በልፋት የተዘራውም ተስፋ ዛሬ ፍሬ ማፍራት ጀምሯል፡፡

በኃይለኢየሱስ መኮንን

Exit mobile version