አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እንጅባራ ከተማ የሚገኘው የአገው ምድር 2ኛ ከፍተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዋ ሕዳሴ ዘመኑ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 583 በማምጣት 2ኛውን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች፡፡
በስሟ ቤተ መጽሐፍት የተሰየመላት ጀግናዋ ተማሪ ሕዳሴ ዘመኑ በተፈጥሮ ሳይንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ 2ኛውን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበች ሲሆን÷ በሴቶች ደግሞ 1ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች፡፡
ተማሪ ሕዳሴ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቧ መደሰቷን ለፋና ዲጂታል ገልጻለች፡፡
ለፈተናው ልዩ ትኩረት በመስጠት ቀድማ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋ እንደነበርና በዚህም የድካሟን ፍሬ እንዳገኘች ጠቅሳለች፡፡
በቀጣይ በኮምፒውተር ሳይንስ ሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ትምህርቷን በመከታተል ለሀገሯ የበኩሏን ማበርከት እንደምትፈልግ ገልጻለች፡፡
የተማሪ ሕዳሴ ዘመኑ ወላጅ አባት ዘመኑ ምህረት (ዶ/ር)÷ ልጃቸው ባስመዘገበችው ከፍተኛ ውጤት መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

